ግንቦት 26 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአምና ሻምፒዮኖቹ ሊቨርፑሎች ዘንድሮ ካሳለፉት ደካማ የውድድር ዘመን አንፃር ባለፈው ቅዳሜ አሰልጣኝ አርን ስሎትን ካሰናበቱ በኋላ፣ የቀድሞውን የቦርንማውዝ አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላን በአዲስ መሪነት ለመሾም ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል። የዝውውር ጉዳዮች ተንታኙ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዝውውሩ መቶ በመቶ መረጋገጡን ያበሰረ ሲሆን፥ ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ የተደረጉት ንግግሮች በጥሩ ሁኔታ ተጠናቀው ስምምነት ላይ መደረሱን እና የ43 ዓመቱ ባስካዊ ታክቲሺያን የሊቨርፑልን አዲስ ፕሮጀክት ለመምራት መዘጋጀቱን ገልጿል።
ሊቨርፑል እንደ ሰባስቲያን ሆኔስ እና ፒየር ሴጅ ያሉ አሰልጣኞችን ቢመለከትም፥ ቦርንማውዝን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ስድስተኛ ደረጃ ላይ አቁሞ ለአውሮፓ ውድድር እንዲበቃ ያደረገውን ኢራኦላን እንደ መጀመሪያ ምርጫው ወስዶታል።
ይህ ውሳኔ ላይ የተደረሰውም ከክለቡ የቀድሞ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ መሆኑ ታውቋል።
ከኢራኦላ መጪ ሹመት ጋር ተያይዞ የአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት ዝርዝርም ይፋ እየሆነ የመጣ ሲሆን፥ በቦርንማውዝ አብሮት የነበረው እና በልጅነቱ የሊቨርፑል ደጋፊ እንደነበረ የሚነገርለት የ38 ዓመቱ ቶሚ ኤልፊክ እንዲሁም ሌላኛው ረዳቱ ሻውን ኩፐር አሰልጣኙን ተከትለው አንፊልድ ይደርሳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ከአዲሱ ክለብ ሁኔታ ጋር በፍጥነት ለመላመድ እንዲረዳ ቀድሞ በክለቡ የተጫወተ እና የሊቨርፑል ትስስር ያለው ሰው በአሰልጣኝ ቡድኑ ውስጥ እንደሚካተት የተሰማ ሲሆን፥ ምንም እንኳን የስቲቨን ጄራርድ ስም ቢነሳም የቅርብ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቀድሞው ድንቅ አማካኝ ቲያጎ አልካንታራ ይህንን አዲስ ሚና ሊረከብ እንደሚችል በሰፊው እየተገመተ ይገኛል።
አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ በአጨዋወት ፍልስፍናቸው በተጋጣሚ ላይ ከፍተኛ የሜዳ ላይ ጫና በመፍጠር (high pressing) እና ኳስን በነጠቁ ቅጽበት በቀጥታ ወደ ተጋጣሚ ጎል በሚደረግ ፈጣን ሽግግር (direct vertical transitions) ላይ የተመሰረተ ማራኪ እግር ኳስን የሚያራምዱ በመሆናቸው ይታወቃሉ። በታዋቂው አሰልጣኝ ማርሴሎ ቢዬልሳ ስር ተጫውቶ ማለፉ ለታክቲክ እውቀቱ ትልቅ መሠረት እንደሆነ የሚነገርለት ሲሆን፥ ቡድኖቹ ኳስን በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ላይ በፍጥነት ነጥቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እንዲደርሱ ያደርጋል።
ይህ የኢራኦላ ጠንካራ፣ ጉልበት የሚጠይቅ እና የማያቋርጥ የአጥቂ እግር ኳስ አጨዋወት ፍልስፍና፥ ከቀድሞው አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ “ሄቪ ሜታል” እግር ኳስ ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል በመሆኑ፣ ሊቨርፑልን ወደ ቀድሞው የማጥቃት እና የማሸነፍ ማንነቱ ለመመለስ ፍጹም ተስማሚ ታክቲክ እንደሆነ በስፖርት ተንታኞች ዘንድ ታምኖበታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ