ነሐሴ 06 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)በክረምቱ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አያሌው ከይሳ፤ የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ለአቅመ ደካሞች ተማሪዎች የሚሆኑ የመማሪያ ግብዓቶችን በማሰባሰቡ ሂደት እስካሁን 361 ደርዘን ደብተሮች ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸው፤ 69 እሽግ መጻፊያ እስክሪብቶዎች እና 221 የትምህርት ቤት አልባሳት መሰብሰባቸውን አስታውቀዋል። በቀጣይም የደብተር ቦርሳዎችን እና ሌሎችንም ግብዓቶች በማሰባሰብ ተደራሽ የማድረግ ስራው እንደሚቀጥል አብራርተዋል። አሁን ላይ ወደ 7 ሺህ ለሚጠጉ ተማሪዎች በተለያዩ በጎ ፈቃደኛ መምህራን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች አማካኝነት እየተሰጠ ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት ሲጠናቀቅ፤ ከነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ የትምህርት ቤቶች እድሳት እና የማስዋብ ስራ በስፋት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ በክረምት በጎ ፈቃድ ዘርፍ ላይ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ያብራሩት የሐረሪ ክልል የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ረምዚያ አብዱልዋሃብ፤ በተለይም በትምህርት ዘርፉ ላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሰባሰብ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።
የትምህርት መማሪያ ግብዓቶችን የመግዛት አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የሚውሉ የደብተር፣ የቦርሳ እና የመጻፊያ መሳሪያዎችን ከበጎ ፈቃደኞች በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ የገለጹት ኃላፊዋ፤ ከ8 ሺህ በላይ የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ባለው ስራ መርሃ ግብሩ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ከ40 በመቶ በላይ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
በክረምቱ መርሃ ግብር በተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ከማድረጉም ባለፈ፣ በመንግስት በኩል ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ በጀት ማስቀረት እንደተቻለ ተገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ