ሐምሌ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ፈጥነት ማደጋቸውን ከቀጠሉ፣ እ.ኤ.አ. በ2036 በዓለማችን ላይ የገንዘብ ጥቅም ፈጽሞ ሊያክትም እንደሚችል የቴክኖሎጂው ቢሊየነር ኢሎን ማስክ አስታወቁ።
ማስክ ከ«ዘ ኢኮኖሚስት» (The Economist) መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ እንደገለጹት፣ ሰው መሰል ሮቦቶች እና ኤአይ ሰዎች ከሚጠቀሙበት በላይ ምርትና አገልግሎት በብዛት ማቅረብ በሚጀምሩበት ጊዜ የገንዘብ አስፈላጊነት እየደበዘዘ ይሄዳል። ማስክ «ሁሉም ነገር እንደልብ በሚገኝበት ዓለም ውስጥ ገንዘብ ለምን ያስፈልጋል?» ሲሉ ይጠይቃሉ።
በአዲሱ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ኤአይ አብዛኞቹን የእውቀት ሥራዎች ሲሸፍን፣ ሮቦቶች ደግሞ ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችን በመረከብ የማኑፋክቸሪንግ፣ በትራንስፖርት፣ በሕክምና እና በትምህርት ዘርፎች የሚወጡ ወጪዎችን እጅግ በጣም ያረክሱታል።
የኢሎን ማስክ ራዕይ እንደ ቴስላ ኦፕቲመስ (Optimus) ሮቦቶች፣ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች እና የ xAI ሞዴሎች ባሉ የላቁ ቴክኖሎጂዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ምርቶችና አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ በሚመረቱበት ጊዜ መንግሥታት ለዜጎች በቀጥታ ክፍያዎችን የሚልኩበት አዲስ ሥርዓት ሊፈጠር እንደሚችል የጠቆሙት ማስክ፣ ሆኖም ይህ ሽግግር የሥራ እድሎችን በመቀማትና የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ውዝግቦችን በማስነሳት በኩል ፈተናዎች እንደሚኖሩበት አምነዋል።
በሌላ በኩል፣ ይህ የኢሎን ማስክ የግል ትንበያ እንጂ የተረጋገጠ እውነት አለመሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያሳስባሉ። ሮቦቶች ቢኖሩም እንኳ የመብራት/የኃይል አቅርቦት፣ የመሬት ስፋት እና የሰው ልጅ ትኩረት መጠናቸው የተወሰነ ስለሆነ፣ ሁሉንም ነገር በነፃና እንደልብ ማቅረብ አይቻልም፤ ስለዚህ ገንዘብ አሁንም ያስፈልጋል ሲሉ እየገለጹ ነው፡፡
እንዲሁም የሮቦቶቹ ባለቤትነት በጥቂቶች እጅ የመውደቅ ስጋት በመኖሩ እስከ 2036 ገንዘብ ጥቅሙን ያጣል የሚለው ግምት አሁንም ብዙዎችን አያስማማም ተብሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ