ፌዴሬሽኑ ኮከቡ ኔይማር ጁኒየር ብራዚል ዛሬ በ2026 የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዋን ከሄይቲ ጋር ለምታደርገው መርሀ-ግብር ወደ ፊላደልፊያ እንደማይጓዝ በይፋ አረጋግጧል። ባወጣው መግለጫ መሰረትም፣ የብራዚል ቁጥር 10 እና ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ኔይማር የመጨረሻውን የማገገሚያ ምዕራፍ በተሻለ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ሲል በኒው ጀርሲ እንዲቆይ ተወስኗል።
ኔይማር ብሔራዊ ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ረቡዕ ዕለት በሜዳ ላይ የኳስ ልምምድ የጀመረ ሲሆን፣ ልምምዱንም በሁለት የተለያዩ ክፍለ-ጊዜዎች ከፍሎ አከናውኗል።
በጠዋቱ ክፍለ-ጊዜ ከቡድኑ አጋሮቹ ጋር የመጀመሪያውን የሜዳ ላይ የጋራ ልምምድ ሲያደርግ፣ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በሆቴል ውስጥ በሚገኝ የስፖርት ማዕከል የአካል ብቃት አሰልጣኞችን ክትትል በመታገዝ የጥንካሬ እና የሰውነት ማገገሚያ ስራዎችን ሰርቷል።
የብራዚል ሕክምና ቡድን በተጫዋቹ ላይ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር የሚደረጉ ማናቸውንም አካላዊ ንክኪዎችን፣ ግጭቶችን እና የሜዳ ላይ ሸርተቴዎችን (sliding tackles) በጥብቅ ከልክሏል።
ከተቀናቃኝ ተጫዋቾች ጋር የሚደረግን ግጭት ለማስወገድ ሲባልም ከሄይቲ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ ወደ ፊላደልፊያ እንዳይጓዝ የተደረገ ሲሆን፣ ተጫዋቹ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 17 ወዲህ ምንም ዓይነት ይፋዊ ጨዋታ አላደረገም።
በዓለም ዋንጫው ላይ ለሀገሩ ወሳኝ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲልም አሁን ሙሉ ትኩረቱን በአካል ብቃት ማገገሚያው ላይ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታዋ በሞሮኮ ተፈትና፣ በግብ ዕድል በመፍጠር እና በጨዋታ እንቅስቃሴ ተበልጣ ነጥብ ተጋርታ መውጣቷ ይታወሳል። በመሆኑም ከሄይቲ ጋር ዛሬ ለምታደርገው ጨዋታ የሶስት ነጥብ ማግኘት የግድ የሚላት ሲሆን፣ ይህንንም ያለ ኔይማር ለማሳካት የምትገደድ ይሆናል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ