ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የነዳጅ ምርት የማጓጓዝ ሥራ ከ40 ዓመታት በኋላ በድጋሚ መጀመሩን ገልጿል።
መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው እና ለ17 ዓመታት በባሕር ኃይል ውስጥ በተለያዩ የጦር መርከቦች ላይ ያገለገሉት ሌተናንት ኃለፎም መሰለ፣ ኢትዮጵያ ከአሰብ ወደብ ከመውጣቷ በፊት የነዳጅ ማጣሪያ በአቅራቢያዋ እንደነበራት ያስታውሳሉ። የነዳጅ አቅርቦትን በበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ አሁን ላይ አማራጮችን መፈለግ ግድ እንደሚል ሌተናንት ኃለፎም ጠቅሰው፤ ከናይጄሪያ ነዳጅ የማስመጣት አማራጭ መኖሩ አሁን ላይ የሚበረታታ ቢሆንም፣ ከጂኦግራፊያዊ ርቀቱ አንጻር ኢትዮጵያን ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስወጣ ጠቁመዋል።
አያይዘውም የቀድሞው ባሕር ኃይል ለሀገሪቱም ሆነ ለዓለም አቀፍ መርከቦች አስተማማኝ ዋስትና ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በአዲስ መልክ የተዋቀረ በመሆኑ በተቋሙ በኩል ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው፤ የቀጣናው አለመረጋጋት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር እንደ ናይጄሪያ፣ አንጎላ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን ካሉ የአፍሪካ አገራት ነዳጅን ማምጣት የተሻለ አማራጭ መሆኑን አስገንዝበዋል። ምንም እንኳን የባሕር ጉዞው ረጅም እና ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም፣ አስተማማኝ መንገድ መዘርጋት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት 120 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላንና የናፍጣ ነዳጅ በሦስት ተከታታይ ጉዞዎች ወደ ጅቡቲ ሆራይዘን ተርሚናል ማጓጓዝ መቻሉን ገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ