ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዛሬው ዕለት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አመካካሪዎች ሁለተኛ ዙር ሥልጠናን በአዲስ አበባ አስጀምሯል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከስሜታዊነት ወደ ምክንያታዊ መግባባት ደረጃ እንዲደርስ የአመካካሪዎች ሚና የላቀ ነው ሲሉ የገለጹት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሥፍን አርአያ፣ ይህንንም ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ለዚህም ከዋናው ምክክር በፊት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። የሥልጠናው ዓላማ አመካካሪዎች አካታችና ገለልተኛ የምክክር ሂደት እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸውን ዓለም አቀፍ ዕውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ለማስቻል መሆኑንም ገልጸዋል።
እስካሁን በነበረው ሂደት ኮሚሽኑ በርካታ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙት ቢቆይም፣ አሁን ላይ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መድረሱ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ የተጀመረው የአመካካሪዎች ሥልጠና ለሚቀጥሉት 7 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ ተቀማጭነታቸውን በስዊድንና በኔዘርላንድ አድርገው በሰላምና በግጭት አፈታት ላይ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች ሥልጠናውን እንደሚሰጡ ተገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ