ሰኔ 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) አርሰናል የአጥቂ መስመሩን ለማጠናከር የኖቲንግሃም ፎረስቱን የጨዋታ አቀጣጣይ ሞርጋን ጊብስ-ዋይትን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል፤ ሆኖም ተጫዋቹን ለማግኘት ከፈረንሳዩ ፒኤስጂ (PSG) ከባድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ሲል ፉትቦል ትራንስፈርስ (Football transfers) ዘግቧል።
የ26 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካይ በፎረስት ቤት አስደናቂ እና የተሳካ የውድድር ዓመት ያሳለፈ ሲሆን፣ በ37 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች 15 ጎሎችን አስቆጥሮ 4 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አጥቅቷል። ይህ የጎል ብዛትም በሊጉ ከኦሊ ዋትኪንስ በመቀጠል ሁለተኛው ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ እንግሊዛዊ እንዲሆን አስችሎታል።
ጊብስ-ዋይት ኳስ በእግሩ ስር በሚሆንበት ጊዜ በከፍተኛ በራስ መተማመን እና በቴክኒክ ብቃት የሚንቀሳቀስ ተጫዋች ሲሆን፣ ከተከላካይ የሚመጡ ኳሶችን ወደ አጥቂዎች በማገናኘት ረገድ እጅግ የተዋጣለት ነው። ኳስ ይዞ ወደ ፊት የመግፋት እና የተከላካይ መስመርን የሚሰነጥቁ አስደናቂ ኳሶችን የማስተላለፍ ልዩ እይታ አለው። ኳስ በሌለው ጊዜ ደግሞ በተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች መካከል ያሉ ክፍት ቦታዎችን በፍጥነት በመለየትና በመግባት ረገድ አስደናቂ እንቅስቃሴን ያሳያል። ምንም እንኳን ዋነኛ ሚናው ማጥቃት ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ቡድኑ ኳስ በሚያጣበት ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሶ ኳሶችን በማቋረጥ እና ተከላካዮችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት በማሳየት ውጤታማ እንቅስቃሴ የሚያደርግ መሆኑን ቁጥሮች ያሳያሉ።
ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች እጩ ውስጥ ስሙን ማካተት የቻለው ሞርጋን ጊብስ-ዋይት፣ አምና ቶተንሃምን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። ፎረስት ዘንድሮ በሊጉ እንዲቆይ የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው ይህ እንግሊዛዊ ትሬኳርቲስታ (Trequartista)፣ ሀገሩን በዓለም ዋንጫ እንዲወክል ጥሪ ያልቀረበለት መሆኑ ከፍተኛ ጥያቄ እና ቁጣ ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።
ዘንድሮ ፎረስትን ለቆ ወደ ትልቅ ክለብ የሚያመራበት ጊዜ የደረሰ ይመስላል፤ መዳረሻው የት ይሆናል የሚለው ርዕሰ-ጉዳይም በቀጣይ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ