ሰኔ 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ቼልሲዎች ግብ ጠባቂ ፍለጋ ወደ ገበያው መውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ዋና ትኩረታቸው የሆነውን ማይክ ሜኞን ለማስፈረም ያላቸውን ፍላጎት በድጋሚ መቀስቀሳቸው ተጠቁሟል።
ይህንን መስመር ማጠናከር እንዳለባቸው እና በስፔናዊው ሮበርት ሳንቼዝ ላይ እምነት መጣል ሞኝነት መሆኑን በተደጋጋሚ የእግር ኳስ ተንታኞች፤ የዝውውር ኤክስፐርቶች እና የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ የቀድሞ አንጋፋ ተጫዋቾች ቢያነሱትም፥ በክለቦች ዓለም ዋንጫ ላይ ሮበርት ሳንቼዝ ያሳየው አመርቂ እንቅስቃሴ ያታለላቸው በሚመስል መልኩ ሌላ ግብ ጠባቂ ለማስፈረም የነበራቸውን ፍላጎት ማቀዝቀዛቸው ይታወሳል።
ዘንድሮ ሳንቼዝ በፕሪሚየር ሊጉ አንፃራዊ በሆነ መንገድ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ጥሩ አቋም ቢያሳይም፥ አሁንም በውሳኔ አሰጣጥ (Decision making) ላይ ትልቅ ክፍተቶች እንዳሉበት በተደጋጋሚ እየታየ ይገኛል።
ታዲያ አሁን ሰማያዊዎቹ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ቁጥር አንዱን ግብ ጠባቂ ማይክ ሜኞን ለማስፈረም የነበራቸውን ፍላጎት በድጋሚ በማቀጣጠል ያቀረቡት የ15 ሚሊዮን ፓውንድ የመጀመሪያ ዙር ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል።
የጣሊያኑ ክለብ የዚህን የሦስት እጥፍ ወይም 45 ሚሊዮን ፓውንድ እየጠየቀ ይገኛል። ሜኞ ባለፈው ጥር ወር ከሮሶኔሪዎቹ ጋር ለተጨማሪ 5 ዓመታት የሚያቆየውን ውል መፈረሙ የሚታወስ ቢሆንም፥ ይህ የዝውውር ገበያውን ዋጋ ለመጨመር እና ሚላንን ለመጥቀም ካልሆነ በቀር 5 ዓመት ሙሉ በጣሊያን ይቆያል ማለት አይደለም።
ተጫዋቹ አምና በሁሉም ውድድሮች ባደረጋቸው 48 ጨዋታዎች 44 ጎሎች የገቡበት ሲሆን፥ በ13 ጨዋታዎች ላይ መረቡን ሳያስደፍር (Clean sheet) ወጥቷል። 135 ሙከራዎችንም በማዳን በሴሪያው ቀዳሚ ከሚባሉት ግብ ጠባቂዎች መካከል ስሙ ይጠቀሳል።
ከእነዚያም መካከል በሴሪያው ከፊዮሬንቲና ጋር 2 እኩል ባጠናቀቁበት መርሐግብር 7 ኳሶችን በማዳን የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠበትን አጋጣሚ መጥቀስ ይቻላል።
ተጫዋቹ በቡድን አመራር ክህሎቱም ይታወቃል።
ከፒተር ቼክ እና ቲቦ ኮርቱዋ በኋላ አስተማማኝ ግብ ጠባቂ ያጡ የሚመስሉት እና በዚህ ቦታ ላይ በሚንጸባረቀው ክፍተት ክፉኛ እየተጎዱ የሚገኙት ቼልሲዎች፥ ቦታውን ጥሩ አቅም ባለው ግብ ጠባቂ ማጠናከር የመጪው ክረምት ትልቁ የቤት ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና፥ ከባየር ሙኒክ ወደ ቼልሲ የተመለሰው ሴኔጋላዊው አጥቂ ኒኮላስ ጃክሰን የቀጣይ ዓመት የዣቪ ዕቅድ ውስጥ እንደሚገኝ እና ከዴላፕ ይልቅ የጃክሰን የጨዋታ ትስስር (Link up play) እንዲሁም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አዋጭ እንደሆነ እንደሚረዳ የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ