ግንቦት 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአፍጋኒስታን የሚገኘው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እና ስራ አጥነት ወላጆችን አስገዳጅ እና ልብ ሰባሪ ውሳኔዎች ላይ እየጣላቸው ይገኛል።
በጎር ግዛት የሚኖሩት ሰኢድ አህመድ የተባሉ አባት ያጋጠማቸው እውነተኛ ታሪክ ለዚህ ማሳያ ሆኗል።
የአምስት ዓመት ሴት ልጃቸው ሻይቃ በጽኑ ታማ አስቸኳይ ቀዶ ጥገና ቢያስፈልጋትም፣ አባትየው ግን የህክምና ወጪውን የሚሸፍኑበት ምንም ዓይነት ገንዘብ አልነበራቸውም።
ልጃቸውን ከሞት ለማዳን ያደረጉትን ከባድ ምርጫ ሲያስረዱም “የህክምና ወጪውን ለመክፈል ምንም ገንዘብ ስላልነበረኝ ልጄን ለዘመዴ ለመሸጥ ተገደድኩ” ብለዋል።
እንደ ዘገባዎች መረጃ ከሆነ አባትየው ልጃቸውን ለቅርብ ዘመዳቸው በ200 ሺህ አፍጋኒ (በግምት 3,200 የአሜሪካ ዶላር) ለመሸጥ ተስማምተዋል። በዚህ ስምምነት በተገኘው ገንዘብም የልጅቷ ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ሊከናወን ችሏል።
ነገር ግን ህጻኗ ወዲያውኑ ከቤተሰቦቿ እንዳትለይ ለማድረግ አባትየው አስገራሚ ድርድር አድርገዋል።
በስምምነቱ መሰረት ዘመዳቸው የህክምና ወጪውን ቅድሚያ እንዲሸፍን እና ቀሪው ክፍያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ተከፋፍሎ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል። ይህ ስምምነት ህጻኗ ለጊዜውም ቢሆን ከአባቷ እና ከእናቷ ጋር እንድትቆይ እድል ሰጥቷታል።
አባትየው ይህንን ውሳኔ ለመወሰን የተገደዱት ቀዶ ጥገናው ባይደረግ ኖሮ ልጃቸው ህይወቷ እንደሚያልፍ ስላወቁ እና እሷን በህይወት ለማቆየት ብቸኛው አማራጭ ይህ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባለው ከፍተኛ የድህነት፣ የረሃብ እና የመድኃኒት እጥረት ምክንያት የህጻናት ሞት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ