ግንቦት 04 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ካመለከቱ ድርጅቶች መካከል 55ቱ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ማግኘታቸው ይታወቃል። ፈቃድ ካገኙት ታዛቢዎች መካከል የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አንዱ ሲሆን፤ በመላው ሀገሪቱ ታዛቢዎች እንደሚኖሩት ለጣቢያችን አስታውቋል።
አካል ጉዳተኞች ድምጽ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በመመረጥ እና በምርጫ ታዛቢነትም ተሳትፎ ሊኖራቸው የሚገባ በመሆኑ፤ ዘንድሮ በታዛቢነት የሚሳተፉት አካል ጉዳተኞች ቁጥር በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ታዛቢ ከነበሩት ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ ገልፀዋል። ፌዴሬሽኑ 1 ሺህ 472 አካል ጉዳተኛ ታዛቢዎችን መልምሎ ለምርጫ ቦርድ በማቅረብ ፈቃድ ማግኘቱንም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በምርጫ ጣቢያዎች ከሚያስፈጽሙ ሶስት ሰዎች አንዱ አካል ጉዳተኛ እንዲሆን ጥረት ሲደረግ መቆየቱንና በተወሰኑ ጣቢያዎችም ይህንን ማሳካት እንደተቻለ ተናግረዋል። በዘንድሮው የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ፤ የምርጫውን አፈፃፀም በመገምገም በቀጣይ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት እንደሚሰራበትም አመላክተዋል።
በመላው ሀገሪቱ ለታዛቢነት የተመረጡ አካል ጉዳተኞች በዚህ ሳምንት ስልጠና እንዲወስዱ እንደሚደረግም ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ