ግንቦት 04 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ቡድናቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠመው የዋንጫ እጦት በክለቡ ያልተለመደ እና እንግዳ ነገር መሆኑን በመጥቀስ፣ ጆዜን በድጋሜ የመሾም ፍላጎት ማሳየታቸውን ተነባቢው አምድ MARCA መዘገቡ ይታወሳል።
ፔሬዝ ከጆዜ ጋር ያልቋጩት የቤት ሥራ እንዳለ ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪ የ”ሎስ ብላንኮሶቹ” የመልበሻ ክፍል ከየትኛውም ጊዜ በላይ በተጫዋቾች እብሪተኝነት የተወጠረ መሆኑ እና ተጫዋቾች እርስ በእርስ ለግጭት እየተጋበዙ ያሉበት ሁኔታ መኖሩ ይነገራል። ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለማረጋጋት የሚያስችል አቅም ያላቸው ጆዜ በመሆናቸው፣ ፔሬዝ በጥብቅ ጆዜን በድጋሜ ክለቡን በአሰልጣኝነት እንዲረከቡ ይፈልጋሉ።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ የአውሮፓው ሀያል ቡድን ወደ ቀድሞ ክብሩ እና ገናናነቱ እንዲመለስ መፍትሔ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተሰምቷል።
ሪያል ማድሪድ በአሁኑ ወቅት በአልቫሮ አርቤሎዋ እየተመራ ቢሆንም፣ ቡድኑ ከየትኛውም የዋንጫ ውድድር ውጪ መሆኑን ተከትሎ፣ እንዲሁም ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ከዋንጫ መራቁ በአዲሱ የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ እንዲፈልግ አስገድዶታል።
ምንም እንኳን ቀደም ሲል እንደ የርገን ክሎፕ እና ዲዲየር ዴሾ ያሉ አሰልጣኞች ስማቸው ቢነሳም፣ አሁን ላይ ግን የቀድሞው አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ወደ ሳንቲያጎ ቤርናቦ የመመለስ እድላቸው ሰፊ መሆኑን የማርካ ዘገባ ያመለክታል።
ሞሪንሆ በአሁኑ ወቅት የቤንፊካ አሰልጣኝ ቢሆኑም፣ በክረምቱ በነፃ የመልቀቅ እድል ስላላቸው እና ከፕሬዝዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ጋር ያላቸው መልካም ግንኙነት ለዳግም ሹመታቸው በር ከፋች ሆኗል።
“The Special One” ወይም ራሳቸውን “ልዩው ሰው” እያሉ የሚጠሩት ጆዜ ሞሪንሆ፣ ከዚህ ቀደም በሪያል ማድሪድ ቤት በነበራቸው የሦስት ዓመታት ቆይታ (ከ2010-2013) በአጠቃላይ 178 ጨዋታዎችን መርተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በ128ቱ ድል ቀንቷቸዋል፤ 28 ጊዜ አቻ ሲወጡ፣ በ22ቱ ብቻ ሽንፈት አስተናግደዋል። ይህም 71.9% የማሸነፍ ንፅፅር ያለው ቡድን መገንባታቸውን ያመላክታል።
በሳቸው አመራር ማድሪድ 475 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ 168 ግቦች ብቻ ተቆጥረውበታል።
በስኬት ረገድ ሞሪንሆ በ2011/12 የውድድር ዘመን ሪያል ማድሪድን የታሪክ ከፍተኛ የሆነውን የ100 ነጥብ ክብረ ወሰን በማስመዝገብ የላሊጋው ሻምፒዮን ማድረግ ችለዋል።
በተጨማሪም በ2010/11 የኮፓ ዴል ሬይ ዋንጫን፣ እንዲሁም በ2012 የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫን ለክለቡ አስገኝተዋል። በተለይም ባርሴሎና የበላይነቱን ይዞ በነበረበት ወቅት ማድሪድን ዳግም ተፎካካሪ በማድረጋቸው እና ቡድኑን እስከ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ እንዲጓዝ በማድረጋቸው ይታወሳሉ። አሁን ላይም የሪያል ማድሪድ ቦርድ የክለቡን መንፈስ ለማነቃቃት የሞሪንሆ መመለስ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል።
ማድሪዶች በፕሬዝዳንታቸው አማካኝነት በይፋ ጆዜን ያነጋገሩ ሲሆን፣ ጆዜም የሁለት ዓመት ውል ብቻ እንደሚፈልጉ እና በተጫዋቾች መልበሻ ክፍል ላይ ሙሉ ስልጣን እንዲኖራቸው፣ ከዚህ በተጨማሪ እስከ 10 የሚጠጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማቅረባቸው ታውቋል። ይህንን Football Espana በግንባር ገጹ ይዞት የወጣው መረጃም ያመላክታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ