መስከረም 06 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ) ቻይና በባሕር ውስጥ ምርምር እና የደኅንነት ቁጥጥር ዘርፍ አዲስ እምርታ ያሳየችበትንና የሰው ልጅ ቀጥተኛ እጅ ሳይኖርበት በራሱ የሚንቀሳቀስ አስደናቂ የሮቦት ዓሣ ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጋለች ይህ ቴክኖሎጂ የውሃ ውስጥ መሠረተ ልማቶችን ለመከታተል፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለስለላ ስራዎች ከፍተኛ አቅም እንዳለው ተገልጿል።ይህ አዲስ የባዮሚሜቲክ (Biomimetic) የሮቦት ዓሣ ዲዛይኑ “ጎልደን አሮዋና” (Golden Arowana) የተባለውን እውነተኛ የዓሣ ዝርያ ሙሉ በሙሉ አስመስሎ የተሰራ ነው። ከተለመዱት የውሃ ውስጥ ድሮኖች በተለየ መልኩ ድምፅ የሚያወጣ መካኒካል ፕሮፔለር (Propeller) የማይጠቀም ሲሆን፣ ይልቁንም ባለ 3 መጋጠሚያ የጅራት ክፍሉን በመጠቀም ልክ እንደ እውነተኛ ዓሣ በጸጥታ እና በነፃነት ይዋኛል። ይህ ድምፅ አልባ ተፈጥሮው በባሕር ውስጥ ያሉ ፍጥረታትን ሳያባርር እና ሳይረብሽ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እንዲሁም በማንኛውም የራዳርና የሶናር መሣሪያ ሳይታወቅ የደኅንነት ቅኝት ለማድረግ ያስችለዋል። ሮቦት ዓሣው በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የሶናር የዕይታ ሲስተም የተደገፈ በመሆኑ፣ በውሃ ውስጥ ያሉ እንቅፋቶችን በራሱ በመለየት አቅጣጫውን የመቀየር ብቃት አለው። ይህም ያለ ሰው ረዳት ለረጅም ሰዓታት በውሃ ውስጥ እየተዘዋወረ ምስሎችን፣ የውሃውን ጥራት እና ልዩ ልዩ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ወደ መቆጣጠሪያ ማዕከሉ በቀጥታ እንዲያስተላልፍ ያደርገዋል። ይህ ቴክኖሎጂ በቅርቡ በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት (CIFTIS) ላይ ቀርቦ የበርካታ የሳይንስ ባለሙያዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን፣ በቀጣይም በከፍተኛ ወንዞች እና ግድቦች ላይ ለብክለት ቁጥጥር እና ለመሠረተ ልማት ደኅንነት በሰፊው ጥቅም ላይ እንደሚውል ታውቋል።
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ