ሕዳር 03 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአፍሪካን የቆዳ፣ የጨርቃጨርቅ፣ የአልባሳት እና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ ምርቶች ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ እንዲሁም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያለሙት 12ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ እና ፋሽን ዊክ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንፈረንስ እንዲሁም 15ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ አውደ ርዕይ ዛሬ ሕዳር 3 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ የስብሰባ ማዕከል (አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል) በይፋ ተከፍተዋል።

በኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር እንዲሁም በጀርመን እና በኬንያ በሚገኘው ትሬድ ኤንድ ፌርስ ግሩፕ (Trade and Fairs Group) ትብብር የተዘጋጁት እነዚህ አውደ ርዕዮች እስከ ሕዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቆዩ ሲሆን፣ አፍሪካውያን አምራቾችን፣ አቅራቢዎችን፣ ዲዛይነሮችን እና ባለሀብቶችን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር በማስተሳሰር ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራሉ።
በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ ዳጋቶ ኩምቤ፣ የትሬድ ኤንድ ፌርስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዓለም ትልቁ የንግድ ትርኢት አዘጋጅ ድርጅት “ሜሴ ፍራንክፈርት” የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ተወካይ ስካንደር ነጋሲ እንዲሁም የኢትዮጵያ፣ የጀርመን፣ የኬንያ እና የአፍሪካ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ኢንዱስትሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ከ70 በላይ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ከ250 በላይ አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች (ኤግዚቢተሮች) ምርቶቻቸውን ይዘው የቀረቡ ሲሆን፣ ከ6 ሺህ በላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ላኪዎች፣ አስመጪዎች፣ ገዢዎች እና ባለሀብቶች ኤግዚቢሽኑን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአውደ ርዕዩም ከጥሬ ቆዳ ዝግጅት እስከ ተጠናቀቁ የምርት ውጤቶች ማለትም ጫማ፣ ቦርሳ፣ አልባሳት እና የቆዳ ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎች ድረስ ያሉ የተለያዩ የእሴት ሰንሰለቶች ቀርበዋል።

ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን በሚካሄዱ የኮንፈረንስ መድረኮች የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው ሚና፣ የአውሮፓ ኅብረት ዘላቂ የአቅርቦት ሰንሰለት መስፈርቶች፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው የቆዳ ምርት ለዓለም አቀፍ የቅንጦት ገበያ ማቅረብ እንዲሁም የኢ-ኮሜርስ ንግድ እድገት በስፋት ይዳሰሳሉ። በተጨማሪም አፍሪካውያን እና ዓለም አቀፍ ዲዛይነሮች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው አራት ልዩ የፋሽን ትርኢቶች በመድረኩ ላይ ይካሄዳሉ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ