ሰኔ 19 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የሁለተኛ ዲግሪ (Master’s Degree) የትምህርት ቆይታ ጊዜ ወደ አራት ዓመት ሊያድግ ነው በሚል በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር የነበረው መረጃ ፍጹም ከእውነት የራቀ እና በአረዳድ ስህተት ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አስታውቋል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባወጣው አስቸኳይ ማሳሰቢያ፣ በትምህርት ቆይታው ላይ ምንም ዓይነት የተቀየረ ደንብም ሆነ መመሪያ አለመኖሩን በይፋ አረጋግጧል።
የመረጃው መነሻ ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የተነሳ ሐሳብ ነው። በወቅቱ ከኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ጋር ተያይዞ የቀረበውን ማብራሪያ አንዳንድ አካላት በተሳሳተ መንገድ በመረዳት የሐሰት ወሬውን እንዳሰራጩት ተገልጿል።
ይህ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የዋለው መረጃ ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን በጥብቅ ያሳሰበው የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን፣ ሕብረተሰቡም ሆነ የትምህርት ማኅበረሰቡ በእንደዚህ ዓይነት ያልተረጋገጡ ወሬዎች እንዳይደናገሩ ጥሪ አቅርቧል። ለተጨማሪ እና ትክክለኛ መረጃም በሥራ ላይ የሚገኘውን “የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ደንብ ቁጥር 561/2016” መመልከት የሚቻል መሆኑን ባለሥልጣኑ አያይዞ ገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ