ሰኔ 16 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)የዓለማችን የቴክኖሎጂ ተቋም የሆነው ሁዋዌ (Huawei Ethiopia Enterprise Business Group) የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ወደ ዲጂታል ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ ታላቅ የፋይናንስ ጉባኤ (Huawei Finance Summit 2026) በአዲስ አበባ ሸረተን ሆቴል አካሂዷል። ይህ “Advancing Fintelligence, Shaping Smarter Ethiopia Finance” በሚል መሪ ቃል የተሰናዳው ጉባኤ፥ የሀገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ መሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና የዘርፉን ከፍተኛ ባለሙያዎች በአንድ መድረክ ያገናኘ ትልቅ ሁነት ነበር።

በዚሁ ሙሉ ቀን በተካሄደው ስብሰባ ላይ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ ክላውድ ኮምፒዩቲንግ (Cloud Computing) እና ቀጣዩ ትውልድ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች የኢትዮጵያን የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥ እንዴት ማዘመን እንደሚችሉ ሰፊ ውይይትና ትንተና ተደርጎበታል። በተለይም በ AI የታገዘ የባንክ አገልግሎት ሽግግር፣ በክላውድ የተደገፈ አስተማማኝ የፋይናንስ ሥርዓት ግንባታ እና የሕገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውርን (AML) ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።
የሁዋዌ ኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ (CEO) ጂም ቼን በጉባኤው ላይ እንደገለጹት፥ መድረኩ ሁዋዌ የኢትዮጵያን ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ባላቸው ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማብቃትና የሀገሪቱን ዲጂታል የፋይናንስ ሽግግር ለማፋጠን ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይ ነው። በጉባኤው ላይ እንደ ቴሜኖስ (Temenos) እና ኬይረስ (Keyrus) ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አጋሮችም የተሳተፉ ሲሆን፥ አዳዲስ አረንጓዴ የመረጃ ማዕከላት (Green Datacenters) እና የማሰብ ችሎታ ያላቸው የባንክ ቅርንጫፎች ዲዛይን ላይ ያተኮሩ የላቁ አቀራረቦች ቀርበዋል።

ይህ የፋይናንስ ሰሚት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ በሆነው የባንክና ፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የቴክኖሎጂ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማት እና የደህንነት ዲዛይን ጥምረት ምን ያህል የላቀ ደረጃ ላይ እንደደረሰና የወደፊቱ የዲጂታል ፋይናንስ ጉዞ ምን እንደሚመስል ማሳያ ሆኖ መጠናቀቁ ተመልክቷል።
ምላሽ ይስጡ