ሰኔ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ከ30 በላይ ሀገራትን የወከሉ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት 10ኛው የምስራቅ አፍሪካ የበጎ አድራጎት ጉባኤ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ወጥቶ የራስን አቅም ስለመጠቀም በሰፊው ከመከረ በኋላ ትላንት በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል መጠናቀቁ ታውቋል።
“የሽግግር ሥርዓቶችን በአስተማማኝ መሠረት ላይ መገንባት” በሚል መሪ ቃል ለተከታታይ ቀናቶች የተካሄደው ይህ ታላቅ ጉባኤ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየቀነሰ የመጣውን የውጭ እርዳታ ለመተካት የሀገር ውስጥ የበጎ አድራጎት አቅምን ማሳደግና ስልታዊ አሠራር መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አስምሮበታል። በጉባኤው ላይ የተገኙት የዘርፉ መሪዎች፣ የሲቪል ማኅበራት ኃላፊዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለሀብቶች እና ወጣት መሪዎች ቀጠናው ከተረጂነት አስተሳሰብ ወጥቶ የውስጥ ሀብትንና የዲያስፖራውን አቅም በተደራጀ ሥርዓት መጠቀም የሚችልበትን ስትራቴጂ ነድፈዋል።
በጉባኤው ጎንዮሽ መግለጫ የሰጡት በአፍሪካ የሲቪል ማኅበራት ኅብረት (ሲሲአርዲኤ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሥ ለገሰ፣ ከውጭ በሚገኝ ዕርዳታ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኝ መሆን አህጉራዊ የቤት ሥራዎችን በአግባቡ እንዳይሠሩ ማነቆ እየሆነ መምጣቱን በግልጽ ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ አፍሪካውያን የሀገር ውስጥ ሀብትን በማስተባበር ረገድ ከኢትዮጵያ ትልቅ ተሞክሮ መውሰድ እንደሚችሉ የጠቀሱ ሲሆን፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያለ ምንም የውጭ ሳንቲም በሕዝብ አስተዋጽኦ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫ በመሆኑ አፍሪካውያን ከዚህ ተምረው በራሳቸው ሪሶርስ ራሳቸውን ማቋቋም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሲዳርታ ልማት ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ ፍሬሁን ገብረዮሐንስ በበኩላቸው፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ራሳችሁን ቻሉ የሚሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ በመሆኑ የዲያስፖራውን አቅም በሕጋዊ የገንዘብ መላኪያ መስመሮች በኩል ለልማት ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአይሲዳይ (ICDI) ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር፣ የኒር ግሎባል ኔትወርክ (NEAR Global Network) ተወካይ እና የኢትዮጵያ ሎካላይዜሽን ላብ (Ethiopia Localization Lab) ባልደረባ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ መኮንን በበኩላቸው፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ከግሎባል ኖርዝ (ከምዕራባውያን ለጋሾች) የሚመጣው ትራዲሽናል የገንዘብ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ በመምጣቱና ቀጣይነት በማጣቱ ማኅበረሰብን መሠረት ያደረገ ዘመናዊ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሥርዓት በአስቸኳይ መዘርጋት እንዳለበት በሰፊው አብራርተዋል።

ከ32 በላይ ድርጅቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ሎካላይዜሽን ላብ የሀገር ውስጥ መሪነትን እና የፋይናንስ ራስን መቻልን በስፋት እያስተዋወቀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ልዑልሰገድ፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አደጋ መከላከል ኮሚሽን የሰብዓዊ ቀውሶችን በሀገር ውስጥ አቅም ለመፍታት የሚያስችል እና ከህብረተሰቡ፣ ከመንግስትና ከበጎ አድራጊዎች የሚገኘውን ገንዘብ በአንድ ላይ ሰብስቦ (pooled በማድረግ) ለሀገር ውስጥ ተዋንያን የሚያከፋፍልበት ፖሊሲ አርቅቆ ለማፅደቅ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ማድረሱን ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን (አክሶ – ACSO) የራሱን የሎካላይዜሽን ፖሊሲ ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፣ መንግስት ለዚህ ስራ ትልቅ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ማሳየቱን አረጋግጠዋል። አቶ ልዑልሰገድ አክለውም እንደ ቴሌብር እና ባንኪንግ ሲስተሞች ያሉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም ማህበረሰባዊ የገንዘብ ማሰባሰብ (crowdfunding) ስራዎች ቀድሞውኑ መጀመራቸውንና እንደ መቅዶንያ ያሉ ድርጅቶች እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም ከዚህ ጋር ተያይዞ እውነተኛ ድርጅት መስለው ገንዘብ የሚዘርፉ የማጭበርበር ድርጊቶች ስላሉ ህብረተሰቡ ንቁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ከሁሉም በላይ ግን ፕሮጀክቶች ሌላ ቦታ ታቅደው መጥተው ህብረተሰቡ ላይ መጫን የለባቸውም ያሉት ተወካዩ፣ ማህበረሰቡ ከእቅድ ጀምሮ የራሱን ችግር ራሱ ለይቶ ምላሹን ራሱ እንዲመራ (empowered እንዲሆን) ማድረግ ዘላቂነት ላለው መፍትሄ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አስምረውበታል።
የክርስቲያን እፎይታና ልማት ኮሚቴ ከፍተኛ የሥራ መርሃ-ግብር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ አድማሱ በበኩላቸው በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ፣ በሀገር ውስጥ ያለውን የመስጠት ባህል ወደ ተቋማዊ ሥርዓት ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል። ወይዘሮ ፀሐይ በህብረተሰቡ ውስጥ የመረዳዳትና የመስጠት ባህል በከፍተኛ ደረጃ ቢኖርም፣ በሀገራችን ያለው ልማድ ግን ለኢንስቲትዩሽን ሳይሆን በግል ትውውቅ ለግለሰቦችና ለአካባቢ ሰዎች የመስጠት በመሆኑ ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር እና ተቋማዊ እምነትን ለመገንባት ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ለሲቪል ማህበረሰቡ የተሰጠው የተሳሳተ ትርክት ተቀይሮ ህብረተሰቡን ያቀፈ፣ እራሱን እንዲችል የሚያበቃና ለለጋሾች ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡም ተጠያቂ (accountable) የሆነ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስበዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በሀገሪቱ የጉዳትና የመፈናቀል መጠን በመጨመሩ ሁሉም አካል በፒስ ፕሮግራም ውስጥ ገብቶ ሰላም እንዲመጣ መስራት እንዳለበት የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ መንግስትም የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣ፣ እንዲሁም ከአደጋ ስጋት ዝግጁነት ጋር ተያይዞ የሚሰበሰቡ ሀብቶች ወደ ተግባር ሲቀየሩ እምነት የሚጣልባቸውን (trustworthy) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመምረጥና በመፈተሽ በጋራ መስራት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ህብረተሰቡም በስሙ የሚመጣን ማንኛውንም ድጋፍ በአግባቡ የመጠየቅና የመከታተል ባህል ሊያዳብር እንደሚገባው ወይዘሮ ፀሐይ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ይህ ዓመታዊ ቀጠናዊ መድረክ በበጎ አድራጎት ዘርፍ ውስጥ የሚነሱ አንጋፋ ተግዳሮቶችን፣ ወቅታዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ ክስተቶችን በጋራ ለመገምገም የተካሄደ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ ያለውን አመኔታና ተዓማኒነት መልሶ ለመገንባት የሚያስችሉ የአሠራር ለውጦች ላይ ትኩረት አድርጓል። ጉባኤው መጠናቀቁን ተከትሎ የተገኙት ግብዓቶች ተግዳሮቶችን በጋራ ለመለየት፣ የተቋማት ትስስር ለመፍጠር እና ዘርፉ በቀጠናው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሮች ውስጥ ያለውን ሚና ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ታምኖበታል።
ምላሽ ይስጡ