ሚያዚያ 16 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት በዋይት ሃውስ ኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካውያን በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በትዕግስት እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህ የዋጋ ጭማሪ ኢራንን ከኒውክሌር ስጋት ነፃ ለማድረግ የሚከፈል አነስተኛ መስዋዕትነት መሆኑን ገልጸዋል። አሜሪካውያን በኢራን ጦርነት ምክንያት ለምን ያህል ጊዜ ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ እንደሚከፍሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዝዳንቱ ለጥቂት ጊዜ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም ለዚህ ዋጋ ምትክ ምን እንደምታገኙ ታውቃላችሁ ሲሉ ጠይቀው አንዱን ከተማችንን ወይም መላውን መካከለኛ ምስራቅ ለማጋየት የምትሞክር የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የሌላት ኢራንን ነው በማለት የውሳኔያቸውን አስፈላጊነት አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጦርነቱን ለማቆምም ሆነ የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ለማድረግ የተቆረጠ የጊዜ ገደብ እንደሌላቸው ገልጸዋል። አትቸኩሉብኝ ያሉት ትራምፕ የቀደሙት የአሜሪካ ጦርነቶች ከዚህ እጅግ የረዘሙ እንደነበሩ አስታውሰዋል። በኢራን አመራሮች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት መኖሩን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ እንደ ድመትና ውሻ እየተጣሉ ነው እኛ ትልቅ ምስቅልቅል ፈጥረንባቸዋል ብለዋል።
አሜሪካ ካቀደቻቸው የጥቃት ኢላማዎች ውስጥ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆኑትን ማውደሟንና በአሁኑ ወቅት የተኩስ አቁም ስምምነቱ የቀጠለው ኢራን የሰላም ፍላጎት ስላሳየች መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በአሁኑ ወቅት በአማካይ ከአራት ዶላር በላይ ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል። የኤነርጂ ሚኒስትሩ ክሪስ ራይት የነዳጅ ዋጋ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ እስከ ሁለት ሺህ ሃያ ሰባት ዓመተ ምህረት ሊዘገይ እንደሚችል ቢገልጹም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንቱ መግለጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጂኦፖለቲካ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ