መጋቢት 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ወደ ጨረቃ በመጓዝ ላይ የሚገኘው የአርቴሚስ 2 (Artemis II) የጠፈር መንኮራኩር፣ ጉዞ ከጀመረ ጥቂት ሰዓታት በኋላ በውስጡ በገጠመው የሽንት ቤት ብልሽት እና በሚያቃጥል ሽታ ምክንያት ጠፈርተኞቹን ለከፍተኛ ስጋት ዳርጓል። ይህ “ዩኒቨርሳል ዌስት ማኔጅመንት ሲስተም” (UWMS) ተብሎ የሚጠራው እና 30 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ዘመናዊ ሽንት ቤት፣ በናሳ ሳይንቲስቶች ለስድስት ዓመታት ጥናት ተደርጎበት በ3ዲ ፕሪንቲንግ ቴክኖሎጂ የታይታኒየም ማዕድንን በመጠቀም የተሠራ ነው።
ብልሽቱ መጀመሪያ ያጋጠመው የፈሳሽ ቆሻሻን (ሽንትን) ወደ ውጭ ማስወገድ ባለመቻሉ ሲሆን፣ ይህም በፓምፕ አለመነሳት እና በቧንቧው ውስጥ በረዶ በመፈጠሩ ምክንያት እንደሆነ ታውቋል። ካናዳዊው ጠፈርተኛ ጄረሚ ሀንሰን እንደገለጸው፣ በመንኮራኩሩ ውስጥ “የሚቃጠል ሽታ” (Burning odor) ተከስቶ የነበረ ሲሆን፤ ሽታውም ለረጅም ጊዜ ሳይሠራ ቆይቶ ድንገት ሲበራ የሚቃጠል ማሞቂያ (Heater) ዓይነት እንደነበር ገልጿል።
ናሳ ይህንን ችግር ለመፍታት መንኮራኩሩን ወደ ፀሐይ አቅጣጫ በማዞር፣ በቧንቧው ውስጥ የረጋውን በረዶ በፀሐይ ሙቀት እንዲቀልጥ አድርጓል። ጠፈርተኞቹ ለተወሰነ ጊዜ የድንገተኛ ጊዜ መጠቀሚያ ቦርሳዎችን (Contingency bags) እንዲጠቀሙ ቢገደዱም፣ በአሁኑ ወቅት ሽንት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መመለሱንና ጠፈርተኞቹም “የእፎይታ” መልዕክት ማስተላለፋቸው ተገልጿል።
ይህ ክስተት ወደ ጥልቅ ህዋ በሚደረጉ ረጅም ጉዞዎች ላይ እንደ ሽንት ቤት ያሉ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስተናገድ አሁንም ትልቅ የቴክኖሎጂ ፈተና መሆኑን አመላካች ሆኗል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ