ሰኔ 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የዳቦ መሸጫ ዋጋ መጨመር እና የግራም መቀነስ እንደሚስተዋል በማህበረሰቡ በኩል ቅሬታ ይቀርባል።
ይህንን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለጣቢያችን በሰጠው ምላሽ፥ በመሸጫ መደብሮች ባለሙያዎችን በተደጋጋሚ በማሰማራት የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
በመሸጫዎቹ ላይ በሚደረገው ቁጥጥር እስካሁን ከግራም በታች የሚሸጥ አምራች አለመገኘቱን በመጥቀስ፥ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከ70 ግራም በታች መሸጥ እንደማይቻል የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ብርሃኑ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ገበያውን ለማረጋጋት ከሸገር እና ብርሃን ዳቦ ማምረቻዎች በተጨማሪ 29 የዳቦ መሸጫዎች በከተማ መስተዳድሩ ለ10 ዓመት ያለኪራይ የመሸጫ ቦታ እና ድጎማ ተደርጎላቸው በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸጡ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ቢሮው የዳቦ ማምረቻዎችም ሆኑ መሸጫዎች በተቀመጠው መስፈርት መሰረት እንዲሸጡ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
በከተማዋ ካለው ፍላጎት አንፃር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዋጋ ማረጋጋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ