መጋቢት 15 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአሜሪካ የነፃነት 250ኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክቶ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስል ያለበት ባለ 24 ካራት የወርቅ ሳንቲም ሊታተም መሆኑ የሕግ ባለሙያዎችን ክርክር ቀስቅሷል።
የሳንቲሙ ንድፍ ፕሬዝዳንቱ በኋይት ሐውስ የሥራ ጠረጴዛቸው (Resolute Desk) ላይ የተቀመጡበትን ምስል የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህ እርምጃ በአሜሪካ ታሪክ በሕይወት ያለ ፕሬዝዳንት ምስል በሳንቲም ላይ ሲያርፍ ከ100 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመዘገብ ክስተት ይሆናል።
ከዚህ ቀደም በ1926 ፕሬዝዳንት ካልቪን ኩሊጅ የሀገሪቱን 150ኛ ዓመት የነፃነት በዓል አስመልክቶ በታተመ ሳንቲም ላይ ምስላቸው መታየቱ ይታወሳል። የአሜሪካ የጥበብ ኮሚሽን የሳንቲሙን ንድፍ ማጽደቁ የተነገረ ቢሆንም፣ ተቺዎች ግን ይህ አሠራር ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይልቅ ወደ ንጉሣዊ አሠራር የሚያደላ ነው በማለት እየተቃወሙት ይገኛል።
የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሳንቲሙ ለመደበኛ መገበያያነት የሚውል ሳይሆን ለመታሰቢያነት ብቻ የሚታተም መሆኑን ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ