መጋቢት 14 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። የኢራን ጦር በደቡባዊ እና መካከለኛው እስራኤል በሚገኙ አካባቢዎች ላይ በርካታ የሚሳይል እና የክላስተር የጦር አውታሮችን (Cluster Warheads) ያካተተ ጥቃት መፈጸሙ ተዘገበ። ይህ ጥቃት የተፈጸመው ኢራን በእስራኤል ከተሞች ላይ በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ማግስት መሆኑ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።
እንደ ዘገባው ከሆነ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው እስራኤል በኢራን ላይ ለፈጸመችው ጥቃት አጸፋ ለመስጠት ሲሆን፣ የኢራን የሚሳይል አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል የሚለውን የአሜሪካ እና የእስራኤልን የደህንነት ግምቶች ውድቅ አድርጓል። ቴህራን የላከቻቸው የሚሳይል ብዛት እና የጥቃቱ ስፋት የኢራን ወታደራዊ አቅም አሁንም ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል።
በእስራኤል ደቡባዊ እና መካከለኛው ክፍሎች በሚገኙ ከተሞች የሳይረን ድምጽ ሲሰማ የቆየ ሲሆን፣ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች የሚሳይል ጥቃቱን ለመመከት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። ይሁን እንጂ የክላስተር ቦምቦች አጠቃቀም በጥቃቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ስፋትና ጉዳት ሊጨምረው እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።
ዋሽንግተን እና ቴል አቪቭ ቀደም ሲል የኢራን የሚሳይል ክምችትና የመምታት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ መመናመኑን ቢገልጹም፣ አሁን የተፈጸመው መጠነ ሰፊ ጥቃት ግን ይህንን መረጃ ጥያቄ ውስጥ ጥሎታል። አሜሪካ እና እስራኤል ለዚህ ጥቃት ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚችሉ ዓለም በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ