በአዲስ አበባ ከተማ የላፍቶ ሰማይ ሥር በሚገኝ አንድ አነስተኛ ቢሮ ውስጥ የሚሰማው የፒያኖ ድምፅ ተራ የሙዚቃ ዜማ አይደለም። ያ ድምፅ መደበኛ ባልሆነ የፍልሰት ጉዞ ውስጥ ተቀጥቅጠው የተመለሱ፣ በደላሎች ተስፋ ተበልተው ባዶ እጃቸውን የቀሩ እና በማኅበራዊ መገለል ስቃይ ውስጥ የነበሩ ሴቶች አዲስ የሕይወት እስትንፋስ ነው። ይህ ስፍራ “ምሳሌ” ሪተርንስ ኤንድ ፖቴንሻል ማይግራንት አርት ኦርጋናይዜሽን ሲሆን፣ በውስጡም እንደ “ሊያ ሻረው” ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተጋላጭ ወገኖችን የታደሰ ታሪክ ይዟል።
የሊያ ታሪክ የብዙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ነጸብራቅ ነው። በአዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለከተማ በድሮው ወረዳ 20 በተሰኘ ቦታ ተወልዳ ያደገችው ሊያ፣ በልጅነቷ ነጭ ጋውን ለብሳ ሰዎችን የምታክም ሐኪም የመሆን ሕልም ነበራት። ይሁን እንጂ የቤተሰብ የመጀመሪያ ልጅ መሆኗ የጫነባት ኃላፊነት እና እናቷ ዳቦና እንጀራ በመሸጥ የምታገኘው ገቢ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር አለመመጣጠኑ ሕልሟን አጨልሞታል።
ሊያ ወደ ፍልሰት ዓለም የገባችው ለእናቷ ባላት ጥልቅ ፍቅር ነበር። “እናቴ የተሻለ ኑሮ እንዲኖረን ወደ አረብ አገር የመሄድ ሐሳብ ነበራት። እኔ ግን እናቴ ከምትሰቃይ እኔ ልጅሽ ልሰቃይ በሚል ነው የሄድኩት” ስትል የመስዋዕትነት ውሳኔዋን ታስታውሳለች። በወቅቱ ዱባይ ሄዶ መሥራት ብቸኛውና አማራጭ የሌለው ሕልሟ ነበር። ሆኖም ጉዞዋን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለማድረግ መወሰኗ ለከፍተኛ ብዝበዛ ዳረጋት። “በእግር ረጅም ጉዞ ከመጓዝ ይልቅ ለጉብኝት በሚል ሰበብ በአውሮፕላን ሄጄ በዛው ጠፍቼ እሠራለሁ በሚል ነው የሄድኩት። አጎቴ የትራንስፖርት ወጪዬን እንዲሸፍን አደረግን፤ ሰርቼ እከፍላለሁ በሚል ተስፋ” ትላለች።
እዚያ እንደደረሰች ግን በደላሎች አማካኝነት ተጠልፋ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ተቀጠረች። የተቀጠረችበት ቤት አራት ወለል (G+4) ያለውና ከአባወራዎቹ ውጭ 11 ልጆችን የምታስተናግድበት ሲሆን፣ ይህን ሁሉ ጫና ለስድስት ወራት ብቻዋን ስትወጣ ቆይታለች። ሆኖም የድካሟን ዋጋ ስትጠይቅ የተሰጣት ምላሽ መራራ ነበር። “የስድስት ወር ደመወዜን ከለከሉኝ፤ ያኔ ነው በደላሎች እጅ ለብዝበዛ ተላልፌ መሰጠቴን የተረዳሁት” ትላለች።
ከዚህ ብዝበዛ ለማምለጥ ስትል ወደ ሱዳን ያመራች ሲሆን፣ እዚያም ለ12 ዓመታት ያህል በመደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ስቃይ ውስጥ ቆይታለች። የሱዳን ግጭት ሲቀሰቀስ ግን ባዶ እጇን ወደ አገሯ ተመልሳለች። በቆየችባቸው 15 ዓመታት ውስጥ ያሳለፈችው መከራ አሰቃቂ ነበር። ሊያ በጉዞዋ ወቅት ያየችውን ግፍ እንዲህ ትገልጸዋለች፦ “በጉዞዬ ወቅት በርካታ ሴቶች በወንዶች ሲደፈሩ አይቻለሁ፤ እኔ ላይ የደረሰውን መከራ መናገር ባልፈልግም፣ መደበኛ ያልሆነ መንገድ የሚያስከፍለው ዋጋ እጅግ አሰቃቂ ነው” ስትል ስለሁኔታው ታብራራለች ።
የአየር ንብረት ለውጥና የሰዎች ዝውውር ስላላቸው ቁርኝት ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የአካባቢ መዛባትና የኢኮኖሚ ቀውስ የዜጎችን የመቋቋም አቅም በማዳከም ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ሲሳይ ያደርጋቸዋል። በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የፍልሰት ጉዳዮች ባለሙያ እንደሚሉት፦ “ፍልሰት በራሱ ለልማት፣ ለዕድገትና ለውጭ ምንዛሬ ለሃገር ጠቃሚ ቢሆንም፣ መደበኛ ያልሆነ መንገድ ሲከተል ግን ለብዝበዛ ያጋልጣል። የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ይህንን ተጋላጭነት በማባባስ ዜጎችን ለሰዎች ዝውውር ወንጀል ተጋላጭ ያደርጋል” ሲሉ ስለሁኔታው ያስረዳሉ።
ባዶ እጇን ወደ አገሯ የተመለሰችው ሊያ፣ የሥነ-አእምሮ ስብራት ደርሶባት ነበር። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ነበር “ምሳሌ” የተባለው ድርጅት የደረሰላት።
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሕይወት ዳግም፣ እንደ ሊያ ያሉ ሴቶች በሙዚቃና በሥነ-ጥበብ አማካኝነት ከደረሰባቸው የስሜት ስብራት እንዲያገግሙ ታደርጋለች።

በኢትዮጵያ በሰው የመነገድ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012፣ በአዘዋዋሪዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይደነግጋል። በዚህም መሰረት ይህን ድርጊት የፈጸመ ሰው ከአስራ አምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከሃምሳ ሺህ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ ይደነግጋል።
እንዲሁም በተጎጂው ላይ ሞት አስከትሎ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሃያ አምስት ዓመት ወይም ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት እና በሃምሳ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ በአዋጁ ተጠቅሷል።
ዜጎች እንደ ሊያ ለብዝበዛ እንዳይዳረጉ ሕጋዊ የፍልሰት መንገዶችን መከተል ወይም በአገር ውስጥ ያሉ የሥራ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚሻል ባለሙያዎች ይመክራሉ። ለዚህም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያመቻቻቸው ሕጋዊ የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አማራጮች ተመራጭ ናቸው።
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (IOM) በኢትዮጵያ በኩል የሚያደርገው ጥረት፣ በተለይም በ“CREATE” ፕሮጀክት አማካኝነት ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማስፈን ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ዛሬ ሊያ በምሳሌ ድርጅት ባገኘችው ሥልጠና ታግዛ በዲዛይን ሥራ ላይ ተሰማርታ ትዳር መሥርታ ሰላማዊ ሕይወት እየመራች ትገኛለች። ይህም ተገቢው ድጋፍ ከተገኘ አገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው።

በአጠቃላይ፣ በሰው መነገድን ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመግታት የመንግሥት ተቋማት፣ እንደ IOM ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የ“ምሳሌ” ዓይነት ተጎጂ-መር ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚኖርባቸው በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
በተለይም ማኅበረሰቡ ለተመላሾች ያለውን ዝቅተኛ አመለካከት በመቀየር፣ አዲስ ተስፋ እንዲሰጣቸው ማድረግ ለተመላሾች መልሶ መቋቋም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ይታመናል። ማንኛውም ዜጋ መረጃ ሲፈልግ 8797 ነፃ የጥቆማ መስመርን ወይም 6073 የፍትህ ቢሮ የጥሪ ማዕከልን በመጠቀም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ማንኛውም ዜጋ መደበኛና ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን በመከተል ወይም አገር ውስጥ ባሉ አማራጮች በመጠቀም ራሱንና አገሩን መለወጥ እንደሚችል ተጠቁሟል።
የሊያ ታሪክ እንዳስተማረን፣ በመደበኛ ያልሆነ መንገድ ውስጥ መከራ ቢኖርም፣ በኅብረትና በፈውስ ድልድይነት ግን የጠፋውን ተስፋ ዳግም ማለም ይቻላል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ