መስከረም 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) አዲስ የወጣ የምርምር ውጤት እንደሚያመለክተው በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ለአእምሮ ጤና እጅግ አሳሳቢ መዘዝ ያስከትላል። ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ የእንቅልፍ እጥረት የአእምሮ ቆሻሻን የማስወገድ ኃላፊነት ያለባቸውን ህዋሳት (ሴሎችን) በማነቃቃት ጤናማ የአእምሮ ክፍልን እንዲያስወግዱ ያደርጋል።
አእምሮን የሚያጸዳው የግሊምፋቲክ ሲስተም በዋነኝነት የሚሠራው በጥልቀት እንቅልፍ ላይ እያለን ሲሆን፣ የምንነቃበት ጊዜ ሲበዛ ወይም በቂ እረፍት ስናጣ፣ የቆሻሻ አጽጂ ህዋሳት (ማይክሮግሊያ) ከመጠን በላይ ይነቃሉ። ይህ ከመጠን ያለፈ መነቃቃት ጎጂ የሆኑ ፕሮቲኖችን ከማስወገድ ይልቅ ጤናማ የሆኑ የነርቭ ግንኙነቶችን (ሲናፕሶችን) መብላት እንዲጀምሩ ያደርጋል፤ ይህም በተለምዶ “አእምሮ ራሱን መብላት” ተብሎ የሚጠራው ሂደት ነው ተብሏል።
ጥናቱ በተለይ አጽንኦት የሚሰጠው ሌላው ነጥብ፣ በየምሽቱ ከስድስት ሰዓት በታች መተኛት የአእምሮን እርጅና በየዓመቱ እስከ ሁለት ዓመት ሊያፋጥነው እንደሚችል ነው። ይህ ማለት ሥር የሰደደ የእንቅልፍ እጦት ያለባቸው ሰዎች የአእምሯቸው የባዮሎጂያዊ ዕድሜ ከትክክለኛው ዕድሜያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀድም ይችላል ነው የተባለው።
ይህ አስደንጋጭ ግኝት ረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የአእምሮ ጤናንና የመረዳት ችሎታን (cognitive health) ለመጠበቅ ጥራት ያለውና በቂ እረፍት ማግኘት ምን ያህል ወሳኝ መሠረት እንደሆነ ያጎላል ተብሏል።
ተመራማሪዎች ለአእምሮ ጤንነት ሲባል በየቀኑ ከ7-8 ሰዓት መተኛት ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ