በክለቦች የውድድር መድረክ ላይ ሁለተኛ እርከን የሚሰጠው የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በሁለት እጅግ አስከፊ የውድድር ዘመንን ባሳለፉ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ማለትም በማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሀም መካከል የሚከናወን ይሆናል።
ሁለቱም ክለቦች ከዚ በፊት ዋንጫውን ከፍ አድርገው ማሳካት ችለዋል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተንሀም እኤአ በ1972 እና በ1984 እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ከ8 አመት በፊት በ2016/17 የውድድር ዘመን በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ስር ዋንጫውን ከፍ አድርገው ማሳካታቸው የሚታወስ ነው።
የዘንድሮው የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በሰሜናዊቷ የስፔን ክፍል ውስጥ በምትገኘው ቢልባኦ ከተማ ከ50 ሺሕ ደጋፊዎች በላይ መያዝ በሚችለው ሳን ማሜስ ስቴዲየም ላይ የሚከናወን ይሆናል።
በሊጉ በርካታ ጨዋታዎችን በመሸነፍ ወደ ታችኛው ሊግ ከወረዱት 3 ክለቦች ብቻ ሻል ብለው የሚገኙት ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሀም አስከፊ እና እጅግ በጣም ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩበህን የውድድር ዘመይ ለመታደግ እንዲሁም በአቋራጭ የቀጣይ አመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በአጠቃላይ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት ሲባል እጅግ ከፍተኛ ትንቅንቅ የሚያደርጉበት ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ከጨዋታው በፊት የዩናይትዱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በሰጠው ሀሳብ 26 ተጫዋቾች ወደ ስፔን ማቅናታቸውን በመግለፅ ጉዳት ላይ የነበሩት ዚርክዚ ፤ ዳሎ እና የሌኒ ዮሮን ግልጋሎት እንደሚያገኙ በመግለፆ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግሯል።
የቶተንሀሙ አቻው አንጅ ፖስቴኮግቹ በበኩሉ የጄምስ ማዲሰን ፤ ኩሉሴቭስኪ እና ቤርግቫልን ግልጋሎት እንደማያገኙ በመግለፆ ክለቡን ከረጅም ጊዜ በኋላ ዋንጫውን እንዲያሳኩ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ይህንን ጨዋታ በመሀል አልቢትርነት ጀርመናዊው ዳኛ ፌሊክስ ዛዋየር የሚመራው ይሆናል።
ከ2012 ጀምሮ በፊፋ ተቀባይነት በማግኘት ጨዋታዎችን ሲዳኝ የቆየው የ43 አመቱ ጀርመናዊ ዳኛ በዚ አመት ፓርክ ዴ ፕሪንስ ላይ የተደረገው የፓሪስ ሴንት ጄርሜ እና አርሰናል የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታን ጨምሮ 7 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ዳኝቷል።
ፌሊክስ ከዚህ በፊት በ2023 በክሮሺያ እና ስፔን መካከል የተደረገውን የኔሽንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን በመሀል ዳኝነት መምራቱ የሚታወስ ሲሆን በስፔን ባስክ ግዛት ቢልባኦ ሜዳ በሆነው ሳን ማሜስ ላይ የሚደረገውን የዘንድሮውን የዩርፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ እንዲመራ በአውሮፓ እግርኳስ አወዳዳሪው አካል ተመርጧል።
ፌሊክዝ ዝዋየር እኤአ በ2005 ከጨዋታ ማመቻቸት ጋር በተያያዘ ቅሌት ውስጥ ወድቆ ለ 6ወር ከዳኝነት ታግዶ እንደነበር አይዘነጋም።
ከ2009-10 ጀምሮ በጀርመን ቡንደስሊጋ ላይ ጨዋታዎችን መምራት የጀመረበት ሂደት አለ ፤ በአማካኝ 4.6 ቢጫ ካርዶችን ይመዛል።
15 ኪሎ ግራም የሚመዝነው እና በአውሮፓ ውስጥ ካሉ የዋንጫ ክብሮች ትልቅ ክብደት ያለውን የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን የትኛው ቡድን ከፍ አድርጎ ያሳካዋል የሚለው በእግርኳስ ቤተሰቡ እጅጉን ይጠበቃል።
ቶተንሀም ከማንቸስተር ዩናይትድ ምሽት 4:00 ሳን ማሜስ ስቴዲየም ላይ ይገናኛሉ።

ምላሽ ይስጡ