በኢትዮጵያ የዓይን ሞራ እና ሌሎች የዓይን ጤና ችግሮችን ለመከላከል እንዲሁም የሕክምና አገልግሎትን ለማዳረስ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎችና ከአጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኪዩር ብላይንድነስ ፕሮጀክት (Cure Blindness Project) ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ዘላለም ሀብታሙ አስታወቁ።
ቀደም ሲል ሂማሊያን ካታራክት ፕሮጀክት (Himalayan Cataract Project) ይባል የነበረው ተቋም በኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተደራሽ ሆኗል። በተጨማሪም ባለፈው አንድ ዓመት የሕክምና ሽፋኑ አነስተኛ በሆነባቸው እንደ አፋር እና ሶማሌ ክልሎች አገልግሎቱን የማስፋት ሥራዎች መከናወናቸው ተመልክቷል።
በ2025 ዓ.ም (እ.ኤ.አ.) ብቻ ከ37 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የዓይን ሞራ ቀዶ ጥገና አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተሰጡ የቀዶ ጥገና አገልግሎቶች ውስጥ አንድ ሶስተኛውን ይይዛል ተብሏል። እ.ኤ.አ. በ2006 የተካሄደ ዳሰሳ ጥናት በኢትዮጵያ ከሕዝቡ ውስጥ 1.6 በመቶ የሚሆነው የዓይን ስውርነት እንዲሁም 3.7 በመቶ የሚሆነው የተለያየ ደረጃ ያለው የእይታ ማነስ ችግር እንዳለበት ያመላክታል። ከዓይን ስውርነት ችግሮች ውስጥም 49.9 በመቶ የሚሆነው በዓይን ሞራ የሚከሰት ሲሆን፣ በትራኮማ ምክንያት የሚመጣ የዓይን ብሌን ጠባሳ እና በመነጽር ሊስተካከሉ የሚችሉ ችግሮችም በስፋት ይስተዋላሉ።
በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ስር የሚገኙ ሰባት የዓይን ሪፈራል ሆስፒታሎችን ጨምሮ የዓይን ሐኪሞችን እና የባዮሜዲካል ቴክኒሻኖችን የማሠልጠን፣ እንዲሁም የሕክምና መሳሪያዎችን እና ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። በቅርቡ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የጤና ጉባኤ ላይ ደግሞ ድርጅቱ እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ በ11 ሀገራት ላይ 115 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶችን ለማፍሰስ እና አንድ ሚሊዮን ሰዎችን የዓይን ቀዶ ጥገና ተጠቃሚ ለማድረግ ቃል መግባቱ ተገልጿል።
የዓይን ጤና ችግር የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የትምህርት፣ የምርታማነት፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ ችግር በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የግል ዘርፉ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተቀናጀ መንገድ መሥራት እንዳለባቸው አቶ ዘላለም ሀብታሙ አጽንኦት ሰጥተዋል። በተለይም የዓይን ጤና አገልግሎቶችን በመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ውስጥ ማዋሃድ እና እንደ ዓይን መነጽር ያሉ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ወይም ከታክስ ነጻ የማድረግ ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተመልክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ