ሚያዚያ 29 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ከሰሞኑ የተደረገውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ፣ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ እስካሁን ምንም ዓይነት ውሳኔ አለመወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ አልተላለፈም ያሉት በቢሮው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው፤ በየትኛውም የትራንስፖርት መስመር ከቢሮው ዕውቅና ውጪ በዘፈቀደ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አሽከርካሪዎችና የትራንስፖርት ማኅበራት ድርጊታቸው ሕገ-ወጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ ጥናት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ ነገር ግን ከወር በፊት የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ወደፊት ሊደረግ የሚችለውን የዋጋ ጭማሪ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሕገ-ወጥ የታሪፍ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ቢሮው የሚያደርገው የቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት አቶ ዳኛቸው፣ ሕግ ተላልፈው ሕዝብን በሚበድሉ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድና አሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ባለንብረቶችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
የስምሪት አለመመጣጠን በሚታይባቸው አካባቢዎች የትራንስፖርት እጥረትን ለመቅረፍ የተለያዩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን እና የኤሌክትሪክ ባሶችን በመመደብ፣ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማመጣጠን እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ከታሪፍ ውጪ ተጨማሪ ክፍያ የሚጠይቁ አሽከርካሪዎች ሲያጋጥሟቸው በቢሮው ነፃ የስልክ መስመር 9417 ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ