መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም (መናኸሪያ ሬዲዮ) በዓሉን አስመልክቶ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ጉዞ የሚያደርጉ ተጓዦች የትራንስፖርት እጥረት እንዳይገጥማቸው እየተሰራ መሆኑን የገለጹት መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የዘመን እና የሰላም ባስ ድርጅቶች ናቸው።
የዘመን ባስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያረጋል ባንቴ፤ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በርካታ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች እንዳሉና ፍላጎቱ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው፤ በጉራጌና በሃዲያ አካባቢዎች በይበልጥ በርካታ ተጓዦች እየተስተናገዱ መሆኑን አብራርተዋል።
ከመስቀል በዓል በኋላም በሃይማኖታዊ ጉዞዎች ምክንያት ወደ ደሴና ጊሸን የሚደረጉ ጉዞዎች ይጨምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ ድርጅቱ ያለውን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተጨማሪ አውቶቡሶችን ያለ ተጨማሪ ክፍያ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ድርጅቱ ከአዲስ አበባ ወደ ሆሳዕና አካባቢ በስፋት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በቀን እስከ 5 ጉዞዎች እየተደረጉ እንዳሉም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም במናኸሪያዎች አካባቢ በርካታ ደላሎች እንደነበሩና ተሳፋሪዎች የመዘረፍና የመጭበርበር ሁኔታዎች በስፋት ያጋጥሟቸው እንደነበር ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት ትኬቶችን በኦንላይን መቁረጥ የሚቻልበትን አሰራር መዘርጋት መቻሉንም አብራርተዋል።
በተመሳሳይ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ተጨማሪ አውቶቡሶች መዘጋጀታቸውን የገለጹት የሰላም ባስ የገበያ ጥናትና የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ኃይለማሪያም፤ ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭና ወላይታ የጉዞ መስመሮች በርካታ ተጓዦች እየተስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አለማድረጉን፤ በርካቶች ከበዓሉ ሁለት ሳምንት አስቀድመው ትኬት መቁረጣቸውን እና እጥረት እንዳይከሰት በእያንዳንዱ ቀን አንድ አንድ ተጨማሪ አውቶቡሶችን ለመመደብ መታቀዱን አስረድተዋል።
የሰላም ባስ ልዩ ባሶችን በመጠቀም ተሳፋሪዎች ሳይጉላሉ ወደሚፈልጉባቸው አካባቢዎች እንዲጓዙ እየሰራ ቢሆንም፤ የደንቢዶሎና ነቀምቴ አካባቢዎችን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የመንገድ መቆፋፈርና ያረጁ የአስፋልት መንገዶች በመኖራቸው ለሥራ ሂደቱ ተግዳሮት መፍጠሩንም አስታውቋል።
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ