ነሐሴ 28 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)
በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ፣ የጉዞና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዘመናዊ የዲጂታል መፍትሔዎችን በማቅረብ የሚታወቀው ዛጎል ሴሊቲዮስ ትራቭል፣ በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መተግበሪያው በሀገሪቱ የቱሪዝም እና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አስታውቋል።
በመግለጫውም አንጋፋው የኪነ-ጥበብ ባለሙያ አርቲስት ዓለማየሁ ታደሰ የዛጎል ሴሊቲዮስ ትራቭል የብራንድ አምባሳደር በመሆን ከተቋሙ ጋር ስምምነት ፈጽሟል።
የዛጎል ሲስተምስ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ ንጉሴ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እና እንደ ኒውዮርክና ጄኔቭ የዓለም ሦስተኛዋ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ከተማ እንደመሆኗ መጠን፣ ወደ ሀገሪቱ ለሚገቡ በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እንግዶች፣ ዲፕሎማቶችና ተጓዦች የተቀናጀ ዲጂታል አገልግሎት ማቅረብ አስፈላጊ በመሆኑ መተግበሪያው በሥራ ላይ ውሏል።
ይህ የተቀናጀ አሠራር ተጓዦች ከዓለም አቀፍ የበረራ ትኬት ቆረጣ እስከ ሆቴል መያዝ (booking) ያሉ ሂደቶችን በአንድ ቦታ በፍጥነትና በጥራት እንዲያከናውኑ የሚያስችል ሲሆን፣ የእንግልትና የጊዜ ብክነትንም ለማስቀረት አስችሏል።
ዛጎል በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገባቸው በርካታ ውጤቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ 60 በመቶ የገበያ ድርሻ በመያዝ በዘርፉ ጠንካራ ተወዳዳሪነትንና መሪነትን መቀዳጀቱ፣ እንዲሁም ከ250,000 በላይ ደንበኞችን በማፍራት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከፍተኛ እምነትን ማትረፉ ተመላክቷል።
በተጨማሪም ከ12 በላይ ዋና ዋና አየር መንገዶች፣ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሆቴሎች እንዲሁም ከ1,500 በላይ የትራንስፖርትና የቱር አቅራቢዎች ጋር ጥምረት መፍጠሩ ተገልጿል።
ኩባንያው ይህንን ስኬቱን ይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ተሻለ ግብ ለመድረስ ከአንጋፋው አርቲስት ዓለማየሁ ታደሰ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ