ነሐሴ 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የፕሮፌሽናል ቦክስ ስፖርትን ለማሳደግና በዘርፉ ያሉ ስፖርተኞችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢቲኤፍሲ (ETFC) መስራችና ባለቤት አቶ ጌታቸው መለሰ ገልጸዋል። አቶ ጌታቸው በቅርቡ የተካሄደው የቦክስ ውድድር በስኬት መጠናቀቁንና በርካታ የስፖርቱ አድናቂዎች የተከታተሉት እንደነበር ተናግረው፤ በዕለቱ በተካሄዱት 11 የቦክስ ፍልሚያዎች ላይ 22 ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸውን እና እንደየደረጃቸው ክፍያ መፈጸሙን ገልጸዋል። በአዳራሽ ውስጥ ከ2,500 እስከ 3,000 የሚደርሱ ተመልካቾች በግንባር ተገኝተው ውድድሩን የተከታተሉ ሲሆን፣ በዲጂታልና በኦንላይን የቀጥታ ስርጭት ደግሞ በርካታ ሚሊዮን አድናቂዎች እንዲሁም ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ተመልካቾች ውድድሩን መከታተላቸውንም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል። ድርጅቱ በቀጣይም የቦክስ ስፖርቱን የበለጠ ለማስፋፋት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ፣ በየሦስት ወሩ ትላልቅ ውድድሮችን፣ በየወሩ ደግሞ ከፊል የማጣሪያ ውድድሮችን ለማካሄድ ማቀዱን እና በዓመት ሁለት ጊዜ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበትን ውድድር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። አዘጋጆቹ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውድድሮች ያገኟቸውን ልምዶች በመጠቀም በቀጣይ የሚካሄዱ ፕሮግራሞችን ይበልጥ ጠንካራ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ውድድሮቹን ወደ 11 ፍልሚያዎች ዝቅ ለማድረግ መወሰናቸውን አብራርተዋል፤ ይህም አሰራር የሀገር ውስጥ ስፖርተኞች ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲወዳደሩና የውጭ ሀገር ተፋላሚዎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ይህም የስፖርቱን እድገትና የሀገሪቱን ቱሪዝም በጋራ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ