ነሐሴ 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ በሚያቆሙ መጋቢ እናቶች ምትክ ከ1 ሺህ 500 በላይ እናቶችን ለመቅጠር ማቀዱን የከተማዋ የምገባ ኤጀንሲ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል። በየዓመቱ በእድሜና በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ የሚለቁ እናቶች በመኖራቸው፣ በእነሱ ምትክ አስፈላጊዎቹን መስፈርቶች የሚያሟሉ ከ1 ሺህ 500 በላይ መጋቢ እናቶችን ለመቅጠር መታቀዱን የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ ማሞ ተናግረዋል፡፡ የኤጀንሲው መስፈርት አንድ መጋቢ እናት ከ50 እስከ 70 ለሚደርሱ ተማሪዎች ምግብ እንድታበስል የሚጠይቅ በመሆኑ፣ እንደ ተማሪዎች ቁጥር የመጋቢ እናቶች መጠንም ሊጨምር እንደሚችል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የምገባ ፕሮግራም እየሰሩ የሚገኙ ከ16 ሺህ በላይ ነባር እናቶችን ብቃትና የምግቡን ጥራት ለማረጋገጥ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ወይዘሮ ስንታየሁ ጠቅሰዋል። በክረምቱ መርሃ ግብር ለእናቶቹ የስልጠና እድል በማመቻቸት፣ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ በማድረግ እና በምግብ ዝግጅት ሥራው የተረጋገጠ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ በየጊዜው የሚስተዋለው የዋጋ ንረት በመጋቢ እናቶች ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ፣ ግብአቶችን በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ከአምራቾች ጋር የገበያ ትስስር መፈጠሩን ያስታወቁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ የምገባ ሥራው እንዳይስተጓጎል በትምህርት ቤቶች የውሃ፣ የመብራት፣ የኃይል ቆጣቢ ኤሌክትሪክ ምድጃዎች እና የመጋዘን አቅርቦት እንዲሟላ መደረጉን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ለእናቶቹ ይከፈል የነበረው ክፍያ መሻሻሉን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፣ አሁንም ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አዲስ ክፍያ እንዲኖር ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የምገባ መርሃ ግብሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የግብዓት ዋጋ አለመረጋጋት ዋነኛው ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸዋል። ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አዲስ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ጥናት እንደተጠናቀቀ ውሳኔው ይፋ እንደሚደረግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ