ነሐሴ 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በምሽትና በርቀት በግልና በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለው የ12ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ 23 ሺህ 281 ተማሪዎች ውስጥ አንድም ተማሪ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አለማምጣቱን አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት በክልሉ ፈተናውን ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያላመጡ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ እንዲል ማድረጉን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ካስፈተናቸው 197 ሺህ 34 ተማሪዎች ውስጥ 10 ነጥብ 53 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ከእነዚህ ውስጥ በመደበኛነት ትምህርታቸውን ተከታትለው ለፈተና ከተቀመጡ 173 ሺህ 753 ተማሪዎች መካከል 12 በመቶ ያህሉ የማለፊያ ውጤት (ከ50 በመቶ በላይ) ማምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም በክልሉ ከመደበኛ ተማሪዎች ውጪ በርቀትና በምሽት ተምረው ፈተናውን ከወሰዱ 23 ሺህ 281 ተማሪዎች መካከል አንድም ተማሪ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አለማምጣቱን ዶክተር ቶላ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህም በክልሉ ያላለፉ ተማሪዎች ቁጥር ከፍ እንዲል ማድረጉን የገለጹት ኃላፊው፣ በመደበኛ ትምህርት ፕሮግራም ውጪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎች በሙሉ አለማለፋቸውን አብራርተዋል፡፡ ምንም እንኳን ከመደበኛ ተማሪዎች ውጪ ያሉት ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ባያመጡም፣ በክልሉ በዘመኑ የተመዘገበው ውጤት ከባለፈው ዓመት የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ክልሉ በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል በማሳለፍ ምጣኔ ቀዳሚ ሲሆን፣ ለፈተና ከተቀመጡት ውስጥ ከ20 ሺህ 877 በላይ ተማሪዎች ማለፋቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ