ነሐሴ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በእንግሊዝ ኬንት ግዛት ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት በኖሩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ የነበሩ ባልና ሚስት፣ በኩሽናቸው ውስጥ በሚገኝ ካቢኔ ጀርባ የታፈነውን ግድግዳ በመስበር ባደረጉት ፍተሻ አስደንጋጭና አስፈሪ ድብቅ ክፍሎችን ማግኘታቸው ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።
ቶም ጎልድ እና ሚስቱ ሳም ጎልድብሮም የተባሉት እነዚህ ባልና ሚስቶች በቤታቸው ካቢኔ ጀርባ በጡብና በፕላስተር ተደፍኖ የቆየ በር መኖሩን ለረጅም ጊዜ ሲያስተውሉ የቆዩ ቢሆንም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ግድግዳውን አፍርሰው ለመግባት ደፍረዋል።
በግድግዳው ቀዳዳ በኩል በፍላሽ በራች በማብራት በተደረገው የመጀመሪያ ፍተሻ ወደ ታች የሚወርድ ጨለማ ደረጃ የተገኘ ሲሆን፣ በጥልቀት ሲገቡ ግን ከቤታቸው ስር የተዘረጋ ረጅም ኮሪደርና በርካታ ሚስጥራዊ ክፍሎች መኖራቸው ታውቋል።
ክፍሎቹ የኤሌክትሪክ መስመርና የውሃ ቧንቧዎች የተቀጠሩላቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ በጥንታዊ ሳጥኖችና ሰነዶች የተሞሉ ነበሩ። ከሁሉም በላይ አስፈሪ የሆነው ክስተት በአንዱ ክፍል ግድግዳና ዝቅተኛ ኮርኒስ ላይ በጨለማ አረንጓዴ ቀለም የተቀቡ የሰው እጅ ምልክቶች ተደርገው መገኘታቸው ነው።
በተጨማሪም በኮሪደሩ መጨረሻ አካባቢ ወደ ውጭ የአትክልት ስፍራ ያመራል ተብሎ የሚገመተው መውጫ መንገድ በጡብና በፍርስራሽ ተደፍኖ ተግኝቷል። ባልና ሚስቱ ይህንን አስደናቂና አስፈሪ ፍተሻቸውን በቪዲዮ ቀርጸው በማህበራዊ ሚዲያ ያቀረቡ ሲሆን፣ አጭር ቪዲዮው በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመልካቾችን በማግኘት ከፍተኛ ትኩረትን ስቧል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ