ሰኔ 19 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በሥነ-አእምሮ ሕክምና ሥራም ሆነ በትምህርት ሂደት ውስጥ “ችግር አለበት” ተብሎ የሚገለል ልጅ ሊኖር እንደማይገባ የገለጹት የአብርሆት ስፔሻላይዝድ የሳይኮሎጂ ማዕከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ኤዶሚያስ ደጀኔ፤ በትምህርት ተቋማትና በማኅበረሰቡ ዘንድ በአካቶ ትግበራ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት በርካታ ሕፃናት ቤት ውስጥ ለመቅረት መገደዳቸውን ገልጸዋል።
የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል ለመማር የሚያስችላቸው አጋዥ የትምህርት ሥርዓት አለመዘርጋቱን የሚያነሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ለእያንዳንዱ ልጅ እኩል የትምህርት ዕድል ሊሰጠው እንደሚገባ አስረድተዋል።
በመሆኑም በመምህራን፣ በተማሪዎችና በወላጆች ዘንድ ስለመማር ዕክል (Learning Disability) ያሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን ከመሙላት አንጻር በርካታ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸው፤ የሚመለከታቸው ተቆጣጣሪ አካላትም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ከአካቶ ትግበራ ጋር በተያያዘ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል። በቢሮው የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትግበራ ባለሙያ የሆኑት አቶ ጸጋዬ ሁሌ፤ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ልዩ ተጠቃሚ ለማድረግ የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ለመደገፍ ለወላጆችም የተለያዩ ሥልጠናዎችን ቢሮው እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቀሱት ባለሙያው፤ ትምህርት ቤቶች የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን በአግባቡ ተቀብለው በተገቢው ሁኔታ እንዲያስተምሩ ክትትል እየተደረገ ቢሆንም፥ አሁንም በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ ክፍተቶች መታየታቸውን አስታውቀዋል።
ይህንንም ክፍተት በዘላቂነት ለመፍታት ቢሮው በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በመሆኑም ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎችን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር እኩል ማስተማር ላይ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ምስል – AI
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ