ሰኔ 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚታዩ የአየር ንብረት እና የመሬት ይዞታ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ ታላቅ ሀገራዊ የፖሊሲ መድረክ በአዲስ አበባ በሚገኘው ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሂዷል። ይህንን ከፍተኛ ውይይት “ላንድ ፎር ላይፍ” (Land for Life – LfL) ኢትዮጵያ ከብሔራዊ የመሬት ጥምረት (National Land Coalition–Ethiopia) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል።
ይህ መድረክ የመንግስት ተቋማትን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ ምሁራንን፣ የአርብቶ አደር ተወካዮችን እና የልማት አጋሮችን በአንድ ጣሪያ ስር ያገናኘ ስብሰባ ነው። በአፍሪካ ቀንድ (IGAD) ቀጠና ውስጥ ከ50 ሚሊዮን በላይ አርብቶ አደሮች የሚኖሩ ሲሆን፥ ይህም የአጠቃላይ አፍሪካ አርብቶ አደር ማህበረሰብ 21 በመቶውን ይሸፍናል። ሆኖም ግን ተደጋጋሚ የአየር ንብረት ድንገተኛ አደጋዎች፣ አስተማማኝ ያልሆነ የመሬት ይዞታ ዋስትና እና የመሬት ሽሚያዎች በአሁኑ ሰዓት በአርብቶ አደሩ ህልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት ከመፍጠራቸውም በላይ ለግጭቶች መነሻ እየሆኑ መምጣታቸው በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

ይህ ከፍተኛ የፖሊሲ ውይይት በቅርቡ የወጣውን አዲሱን የኢትዮጵያ ህጋዊ ማዕቀፍ ወይም አዋጅ ቁጥር 1324/2016 (1324/2024) ላይ በስፋት ትኩረቱን አድርጓል። ይህ አዋጅ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ ግልጽነት የሰፈነበት እና የባህላዊ ተቋማትን እውቅና የሚያጠናክር በመሆኑ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ፍትሃዊ እና ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ለመዘርጋት ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑ ተገልጿል።
የመድረኩ ዋና ዓላማዎች በአርብቶ አደሩ መሬት ይዞታ እና የአየር ንብረት መቋቋም ዙሪያ ሰፊ የፖሊሲ ውይይት ማድረግ፣ በአዲሱ አዋጅ ላይ የተመሰረቱ የውሳኔ ሃሳቦችን ማመንጨት እና የባህላዊ ተቋማትን የጋራ ይዞታ መብት ማጠናከር ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም ቢያንስ 40 በመቶ ሴቶች እና 20 በመቶ ወጣቶች የተሳተፉበት አሳታፊ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፥ ዘላቂ መፍትሄዎችን የያዘ ሀገራዊ የፖሊሲ ሰነድ እና የውይይቱ ዝርዝር ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ እንዲሰራጭ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ የክልል አንጋፋ አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተገኙ ሲሆን፥ በተለይም ሴቶች እና ወጣቶች በጋራ መሬት ይዞታ ስር ሊኖራቸው በሚገባው ሚና ላይ ያተኮሩ ልምዶቻቸውን እና ጠቃሚ እይታዎቻቸውን በማካፈል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ