ሰኔ 17 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ/ም ከምሽቱ 2 ሰዓት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 መስቀል አደባባይ አካባቢ ሲሆን፣ እስጢፋኖስ ተስፋዬ፣ ወንድሙ ደምሴ፣ ቦምሳ አብሳ እና ኢብራሂም አስፋው የተባሉት ተጠርጣሪዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከመጣ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ላይ የስርቆት ወንጀል መፈጸማቸው ተገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ የግል ተበዳዩን “ሶፍት ግዛን” ብለው በማዋከብና ትኩረቱን በመስረቅ፣ ኪሱ ውስጥ የነበረውንና ግምቱ 204 ሺህ ብር የሚያወጣ አይፎን 17 ፕሮ (iPhone 17 Pro) የተሰኘ ስማርት ሞባይል ስልክ ይዘውበት መሰወራቸውን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
በዕለቱ ከግል ተበዳዩ የስልኩ መጥፋት ሪፖርት የደረሰው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፣ የክትትል ቡድን በማቋቋምና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅንጅት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል መጀመሩን ጠቁሟል።
በተደረገው ፈጣን የማፈላለግና የክትትል ስራም፣ አራቱም ተጠርጣሪዎች ስልኩን እንደያዙ ከተኙበት ደምበል ዲሲ ከሚባል አካባቢ በዚያው ሌሊት በሰዓታት ልዩነት በቁጥጥር ስር ውለዋል። የግል ተበዳዩም ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አድማሱ ኢፋ ንብረታቸውን የተረከቡ ሲሆን፣ ፖሊስ ምርመራውን እያሰፋ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ፖሊስ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ያለ እረፍት 24/7 የሚሰራ ቢሆንም፣ ወንጀል ፈጻሚዎች አሳቻ ሰዓት እና ቦታን የሚጠቀሙ በመሆኑ፣ በምሽት ለተለያዩ የግል ተግባራት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ንብረቶቻቸውን በአግባቡ መያዝ እንደሚገባቸውና ወንጀል ሲፈጸምም ወዲያውኑ ለፖሊስ ማሳወቅ እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ