ሰብዓዊ ፍጡር የሆነው የሰው ልጅ በተፈጥሮው በርካታ ድንቅ ስጦታዎች ተሰጥተውታል። ከእነዚህም መካከል ትልቁና የመጀመሪያው የሰውነት አካል የሆነው ቆዳው ነው።
የሰውነት ቆዳ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭ የሚመጡ ማናቸውንም በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን በመከላከል ሕይወትን በውስጡ አስጠብቆ ማቆየት የሚችል ተፈጥሯዊ ምሽግም ነው።
ነገር ግን ይህ ምሽግ በከባድ የኬሚካል ወይም የእሳት ቃጠሎ፣ አሊያም በሌሎች አስከፊ አደጋዎች ሲጎዳ አደጋው ከሚያስከትለው ከፍተኛ ስቃይና ሥነ-ልቦናዊ ስብራት ባሻገር፣ ቆዳቸውን በአደጋ ያጡ ወገኖች የበሽታ የመከላከል አቅማቸው እንደሚዳከም የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
እንደ ደም ባንክ ሁሉ፣ የሰውን ልጅ ሕይወት ለመታደግ የቆዳ ልገሳና ክምችት ወይም “ስኪን ባንክ” እንደሚያስፈልግ በዓለም አቀፍ ደረጃና በሀገራችን ያሉ ሙያተኞች ይናገራሉ፡፡
እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት በአፍሪካ የመጀመሪያውንና ትልቁን የቆዳ ባንክ ካቋቋሙት ተርታ የሚመደቡ ሲሆን፤ በተለይም የቃጠሎ አደጋ ለደረሰባቸው ሕፃናትና አዋቂዎች ከሟቾች የሚገኝን ቆዳ በማከማቸት በስፋት ጥቅም ላይ ያውሉታል።
እንደ ግብፅ ያሉ ሀገራት ደግሞ ለዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያደርጉበት ሲሆን፤ አሜሪካም በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በዚህ ዘርፍ በምትሰጠው ሕክምና ትታደጋለች።
ለመሆኑ ይህ የቆዳ ባንክ አሠራር እንዴት ይከናወናል? ቆዳን ጠብቆ ማቆየትስ እንዴት ይቻላል? ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ እያከናወነቻቸው ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የድንገተኛ አደጋ ቡድን መሪ ዶክተር ባይሳ ጉተታ፤ ሰዎችን ከከፍተኛ አደጋ ለመታደግ የቆዳ ባንክ መኖር ወሳኝ ቢሆንም፣ ብቻውን ግን በቂ አይደለም ብለዋል። ያጋጠሙ ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ ለመሆን 2 ዋና ዋና ክፍተቶች በአስቸኳይ ሊቀረፉ እንደሚገባም ያነሳሉ።
በየካቲት 12 ሆስፒታል የፕላስቲክ እና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ባለሙያ ፕሮፌሰር መኮንን እሸቴ፤ ይህ የሕክምና አገልግሎት ኢትዮጵያ ከምትተገብራቸው የልገሳ ዓይነቶች ወጣ ያለ ነው ይላሉ፡፡
ይህ ባንክ ከሕይወት ማለፍ በኋላ ከሚደረግ የቆዳ ልገሳ የሚገኘውን ቆዳ በከፍተኛ ጥንቃቄ አቀናብሮና ጠብቆ በማቆየት፣ በቃጠሎና በተለያዩ አደጋዎች ለተጎዱ ሕመምተኞች እንደ አዲስ ተፈጥሯዊ መከታ ሆኖ የሚያገለግል ሕክምና መሆኑንም ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ በሕክምናው ዘርፍ ረጅም ዓመታት የቆየ ልምድ ያላት ቢሆንም፤ በአደጋ ወቅት የሚከሰቱ ጉዳቶችን በማከም ረገድ ግን ገና በጅምር ሥራ ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗን ያብራራሉ።
አሁንም ድረስ ዜጎች በሚገጥማቸው አደጋዎች ምክንያት በቆዳቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ወደ ሕክምና ተቋማት እንደሚያቀኑ ገልጸዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፉ አዳዲስ ዕድገቶችን እያሳየ በመምጣቱ፤ ይህን ዓይነቱን አሠራር ወደ ሀገር በማምጣት መተግበር እንደሚገባም አስረድተዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፕላስቲክ እና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንዲሁም በአቤት ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶክተር መታሰቢያ ወርቁ፤ በእሳትና በኬሚካል አደጋዎች ሰውነታቸው ለከፋ ቃጠሎ የሚዳረግ ዜጎች፣ ለከፍተኛ ስቃይ ከመዳረጋቸውም ባለፈ የበሽታ መከላከል አቅማቸው ሙሉ በሙሉ እንደሚዳከም አስታውቀዋል።
ይህንን አስከፊ አደጋ በማከም ሰፊ የሰውነት ክፍላቸው የተቃጠሉ ታካሚዎችን ለመታደግ ትልቁ መፍትሔ “የቆዳ ባንክ” ማቋቋም መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ አሠራር ከፍተኛ ግብዓትና ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ በርካታ ሀገራት ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ መሆናቸውን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ሕዋስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ፤ ተቋማቸው ሊሠራባቸው ከሚገቡ ሥራዎች መካከል ዋነኛው የቆዳ ባንክ አገልግሎት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የሕብረ-ሕዋስ እና የአካል ልገሳ ላይ በስፋት መሥራት ከሚችሉ ተቋማት መካከል አገልግሎቱ ተጠቃሽ እንደሆነም አብራርተዋል። ሕክምናውን በተመለከተም የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን በማንሳት፤ ማዕቀፉ ሲጸድቅ ወደ ተግባር እንደሚገባ አስረድተዋል።
ዘርፉ ሰፊ ግብዓትና የሰው ኃይል አቅርቦት እንደሚፈልግ ተናግረው፤ አገልግሎቱ አሁን ካለበት ደረጃ መሻሻል እንዳለበት ነው ያስረዱት። ሥራው አዲስ በመሆኑ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መስራት እንደሚቀድምም ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያ ቀደም ባሉ ጊዜያት የተለመዱ የአካል ልገሳ ሕክምና አገልግሎቶችን ስትተገብር መቆየቷን ጠቅሰው፤ ይህን ዓይነቱንም አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ዘርፉ እንደ ሀገር አስፈላጊ በመሆኑ እንደ ቅንጦት መታየት የሌለበት እና በፍጥነት ሊተገበር የሚገባው መሆኑን የሚያመላክቱት ባለሙያው፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ጥናት ማድረግ እና በሕግ ማዕቀፍ የማስደገፍ ሥራ መቅደም እንዳለበት አስምረውበታል።
በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ አገልግሎት የድንገተኛና ጽኑ ሕክምና አገልግሎት ዴስክ አስተባባሪ አቶ አማን ሳፉ፤ ትኩረት ከሚፈልጉ የሕክምና ዓይነቶች ውስጥ በቀዳሚነት የቆዳ ባንክ አገልግሎት አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ።
ቀደም ባሉ ጊዜያት ኢትዮጵያ እንደ ደም ባንክ እና ዓይን ባንክ ያሉ ሕክምናዎችን በረጅም ጊዜያት ስታከናውን መቆየቷን በመግለጽ፤ አሁንም ቢሆን በሀገሪቱ ለድንገተኛ ቃጠሎ አደጋ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር ጭማሪ እያሳየ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበሩ የሕክምና ሙከራዎች እዚህም ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ይህ ውድድር በዚህ መልክ ሲካሄድም ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል።
የቆዳ ባንክ መኖር የሰዎችን ሕይወት ለማዳንና ከአደጋ በኋላ የሚከሰቱ ጠባሳዎችንና ስቃይን ለመቀነስ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የሕክምና ባለሙያዎች አመላክተዋል።
ዘመናዊ የሕክምና መሠረተ-ልማትን በመገንባት፣ የቆዳ ልገሳ ባህልን በማዳበር እና አስፈላጊውን የሕግና የሥነ-ምግባር ማዕቀፍ በማውጣት የተሟላ አገልግሎት መስጠት ከተቻለ፣ በአገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ አደጋዎች ሳቢያ የሚቀጠፉ የዜጎችን ሕይወት በከፍተኛ ሁኔታ መታደግ ይቻላል። ስለሆነም፣ ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍና የሚሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በዳሰሳው የተነገረ ሐሳብ ነው።
ሙሉ ዘገባው በድምጽ እዚህ ይገኛል::
ምላሽ ይስጡ