ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የ2018 የትምህርት ዘመን የ6ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ከተማና ክልል አቀፍ ፈተናን በተመለከተ ጣቢያችን የክልል ትምህርት ቢሮዎችን ጠይቋል።
በክልሉ 57 ሺህ 49 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን የገለጹት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገመዳ፤ 26 ሺህ 100 ያህሉ ሴት ተፈታኞች እንደሆኑም ተናግረዋል። ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት ግብረ-ኃይል በማቋቋም ተማሪዎችን የማዘጋጀትና በሁሉም የፈተና መስጫ ጣቢያዎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው፤ ፈተናው ካለፉት ጊዜያት በተሻለ መልኩ ያለምንም ክፍተት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርቶች በሰፊው መሰጠታቸውን ያነሱት ምክትል ኃላፊው፤ በክልሉ ባለው የመጽሐፍ እጥረት ሳቢያ አንድ መጽሐፍ ለሁለት ተማሪ ተደራሽ በማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራው ሲሠራ እንደነበር ተናግረዋል። በተጨማሪም በቀጣይ ለሚደረገው የ8ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ተማሪዎችን የማዘጋጀትና ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም አመላክተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ማቲዮስ ማልዳዮ፤ ፈተናው ከመካሄዱ አስቀድሞ ያለፉ የትምህርት ዓይነቶችን በመከለስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር ተናግረዋል። በክልሉ ፈተናው ያለምንም ችግር መሰጠቱን ገልጸው፤ አስቀድሞ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከ91 ሺህ በላይ ተፈታኞችን መመዝገባቸውን ጠቁመዋል። ከስርቆት ነፃ በሆነ መልኩ ፈተናውን ለመስጠት በታቀደው መሠረት በ881 መፈተኛ ጣቢያዎች ላይ መሰጠቱንም አብራርተዋል።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ፈተና የአዲስ አበባ ከተማን፣ የአማራን፣ የኦሮሚያን እና የጋምቤላ ክልልን ጨምሮ በሌሎችም ክልሎች በትላንትናው ዕለት ተጠናቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ