ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በሳውላ ከተማ ኩስቲ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ፈተና ለተማሪ ሊፈተን ከተማሪ ጋር ተመሳስሎ የገባ መምህር እና ተማሪው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ተማሪውን ወክሎ ከመምህርነት ስነ-ምግባር ባፈነገጠ ተግባር ላይ ተሳትፏል የተባለውና ከቡልቂ ከተማ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው መምህር እስራኤል አሰፋ፣ የማንዴላ ርቀት ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነውን አብነት እንዳለን ተክቶ ክልላዊ ፈተና ሊፈትን ሲል በተደረገ የኮማንድ ፖስት ክትትል በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን የገለጹት የከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያዕቆብ በተላ ናቸው።
ፈተናውን ከኩረጃና ከስርቆት የፀዳ ለማድረግ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ የኮማንድ ፖስት አባላቱ ድርጊቱን በማጋለጥ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠታቸው ሊፈተን የገባው መምህርና ፈተናውን አሳልፎ የሰጠው ተማሪ በቁጥጥር ስር መዋል መቻላቸውን አስረድተዋል።
የሳውላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ምክትል ኢንስፔክተር ሞገስ ሞኔ በበኩላቸው፣ ተማሪውንና መምህሩን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቁመው በማዕከሉ እየተሰጠ ያለው ፈተና ፍጹም ሰላማዊ እና በተረጋጋ መንገድ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ምርመራ በአስቸኳይ አጣርቶ በአቃቤ ህግ በኩል ለፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስወሰን እየሰራ መሆኑንም ምክትል ኢንስፔክተር ሞገስ ሞኔ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ሳውላ ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ