ሰኔ 05 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ድንበርን በጋራ ለማልማትና ለመጠበቅ የሚያስችል ፖሊሲ ማውጣትና ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኟትን ድንበሮች በጋራ ለማስተዳደር በጥናት ላይ የተመሰረተ ፍኖተ ካርታ እየተሰናዳ ስለመሆኑ፣ «የኢትዮጵያን የድንበር አስተዳደር ማጠናከር» በሚል በተካሄደው የጥናት አውደ ጥናት ላይ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ተናግረዋል።
ድንበሮችን ለማስተዳደር ከጸጥታ የተሻገረና ሁሉን አቀፍ ትብብር ማድረግ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከቀጠናው ሀገራት ጋር ለሚታቀደው የንግድ ትስስርና አብሮ የመልማት ሂደት የድንበር አካባቢ ማህበረሰቦችን ደህንነት ያማከለ የሀገራት የጋራ ኃላፊነት ያስፈልጋል ብለዋል።
የድንበር አስተዳደርን ለመምራት የተዘጋጀው አዲሱ ፍኖተ ካርታ ካሁን ቀደም የነበሩ ችግሮችን የሚፈታና የተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጠናክር እንደሆነም ተገልጿል።
ፍኖተ ካርታው ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ህብረትንም በማካተት ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር በማስተሳሰር ድንበርን በጋራ መጠቀምን እውን ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ጎረቤት ሀገራትን ያማከለ በመሆኑ፣ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦችም በፖሊሲው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል ተብሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ