ሰኔ 02 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር በ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ጨዋታዎችን እንዲመራ ተመርጦ የነበረው ታዋቂው ሶማሊያዊ ዳኛ ዑመር አርታን ወደ ሀገር እንዳይገባ መከልከሉን አረጋግጧል።
በፊፋ የዓለም ዋንጫ ላይ እንዲዳኙ ከተመረጡት 52 ዋና ዳኞች መካከል የተካተተውና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) “የዓመቱ ምርጥ ዳኛ” በሚል የሸለመው ዑመር አርታን፣ የመጀመሪያው ሶማሊያዊ የዓለም ዋንጫ ዳኛ ለመሆን ተዘጋጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ ማያሚ (Miami) ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ በኋላ በተደረገበት ጥብቅ የደህንነት ምርመራ ምክንያት ፍቃድ ተከልክሎ ወደ መጣበት ኢስታንቡል እንዲመለስ ተደርጓል። ይህ ውሳኔ የአሜሪካን የጉዞ እገዳ ፖሊሲዎችና በዓለም ዋንጫው ላይ እያሳደሩ ያሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትችት እያስነሳ ይገኛል።
ሶማሊያ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዞ እገዳ ዝርዝር ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ የሙስሊም መብቶች ተሟጋች ተቋማትና የተለያዩ የስፖርት አካላት የተላለፈውን ውሳኔ “አድሏዊ ነው” በማለት በፅኑ አውግዘውታል።
ከዚህ ክስተት በተጨማሪ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ዙሪያ ከአሜሪካ የቪዛና የጉዞ ፖሊሲ ጋር የተያያዙ ሌሎች አወዛጋቢ ሁኔታዎች እየታዩ ይገኛሉ። ለምሳሌ የኢራን ብሄራዊ ቡድን በቪዛ ችግር ምክንያት ዋና ማረፊያና ማሰልጠኛ ጣቢያውን በሜክሲኮ ለማድረግ የተገደደ ሲሆን፣ ተጫዋቾቹ ጨዋታ በሚኖራቸው ወቅት ብቻ ወደ አሜሪካ ገብተው ከተጫወቱ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሜክሲኮ እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሏል። ከዚህም በላይ አንዳንድ የቡድኑ አሰልጣኞችና የቴክኒክ ሰራተኞች የአሜሪካ ቪዛ ሙሉ በሙሉ ተከልክለዋል።
በሌላ በኩል በዓለም ዋንጫው ወቅት የአሜሪካ የስደተኞችና የጉምሩክ አስከባሪ ኤጀንሲ (ICE) በስታዲየሞች ዙሪያ ጥብቅ ፍተሻ እንደሚያደርግ ማስታወቁ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል። የኒውዮርክ ከንቲባ ዞህራን ማምዳኒ ይህንን ውሳኔ በፅኑ በመቃወም፣ ስደተኞች የዚህ ስፖርት የጀርባ አጥንት መሆናቸውንና በደጋፊዎች ላይ ፍርሃት ሊዘራ እንደማይገባ አሳስበዋል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስቴር ግን በማንኛውም ትልቅ የስፖርት መድረክ ስም የሚመጡ እንግዶች በአውሮፕላን ማረፊያ ላይ የሚደረገውን መደበኛ የደህንነት ፍተሻና የቪዛ ውሳኔ እንደማያስቀረው በድጋሚ አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ