ምስሉ ከአምስት ዓመት በፊት በ2013 (2021) በፌስቡክ ላይ የተጋራ የድሮ ምስል ነው።
በቅርቡ በፌስቡክ ማህበራዊ ገጽ ላይ በጆንያ የተሞሉ የምርጫ ካርዶች ምስል በመጋራት፣ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን 7ኛውን የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ለማጭበርበር ካርዶች ተደብቀዋል ወይም ተጥለዋል ተብሎ የተሰራጨው ክስ ውሸት ነው።
“Deriya Affutta” በተባለ የፌስቡክ አካውንት ከተለቀቀው ከዚህ ምስል ጋር አብሮ የቀረበው የጽሑፍ መረጃ “እንግድህ የሙሬ ታዳጊ ማዘጋጃ የምገኙ እያንዳንዱ ምርጫ ካርዶች ከ1,000 በላይ ካርድ በላይ እንደዝህ ሸክፈዉ ለአመራሮች አስረክበዉ አመራሮቹም እንደዝህ ይዘዉ ወስደዋል ነገር ግን ምን ልያደርጉ ነዉ?????” የሚል ክስ ይሰነዝራል። ይህ አሳሳች መረጃ አዲስ የምርጫ ማጭበርበር ወንጀልን እንደሚያሳይ ተደርጎ በሰፊው እንዲሰራጭ የተደረገ ሲሆን፣ ከተለጠፈ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሳሳት መስተጋብሮችን እና ቁጣዎችን ቀስቅሷል።

ኢትዮጵያ 7ኛውን አጠቃላይ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ያካሄደች ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለፌዴራል ፓርላማ እና ለክልል ምክር ቤቶች ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
የእኛ የሀቅ ማረጋገጫ ምርመራ እንደሚያሳየው በስፋት እየተሰራጨ ያለው ይህ ምስል ሙሉ በሙሉ ከአውድ ውጪ የቀረበ እና የሃሰት ነው። ምስሉ የአሁኑን የምርጫ ሂደት የሚወክል ሳይሆን፣ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረ አሮጌ ምስል መሆኑን አረጋግጠናል።
በጉግል የገጽታ ምስል ፍለጋ (Google reverse image search)፣ ያንዴክስ (Yandex) እና ቲንአይ (TinEye) ዲጂታል መሳርያዎችን በመጠቀም የተደረገው ፍለጋ በግልጽ እንደሚያሳየው፣ ይህ በጆንያ የተሞሉ ካርዶች ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ ሚያዝያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም (April 29, 2021) “Armachiho Post” በተባለ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተለጠፈ የድሮ ምስል ነው። ምስሉ የተነሳው ባለፈው የ2013ቱ (2021) ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት እንጂ ለአሁኑ የ2018 (2026) ምርጫ የተዘጋጀ አይደለም።
ይህ ድርጊት የድሮ ምስሎችን አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ ማህበረሰቡን ለማሳሳት የሚደረግ የተለመደ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት (Decontextualized Disinformation) ስልት ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአሁኑ ምርጫ የሚጠቀማቸው የመራጮች ምዝገባ ካርዶች፣ የደህንነት ማህተሞች እና ዲዛይኖች በ2013 (2021) ከነበሩት ቁሳቁሶች ጋር አይመሳሰሉም።
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1 በምስሉ ላይ ዝርዝር ምርመራ ያደረገ ሲሆን፣ ይህ አምስት ዓመት የሞላው አሮጌ ምስል በአሁኑ የምርጫ ሂደት ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር እና የህዝብን አመኔታ ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የሃሰት መረጃ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይላት ወይም የምርጫ አስፈጻሚዎች ካርዶችን በጥቅል ጥለው ማጭበርበር መፈጸማቸውን ለማሳየት በፌስቡክ የተሰራጨውን ምስል መርምረን ሙሉ በሙሉ ውሸት መሆኑን አረጋግጠናል።
በጌታሁን አስናቀ ( By Getahun Asnake)
ምላሽ ይስጡ