ግንቦት 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በየዓመቱ ከሚከናወኑ እና የክለቦች ፉክክር ከሚደምቅበት እንዲሁም በአውሮፓ ውስጥ ሀያሉ ክለብ ለመባል የሚደረግ የክለቦች ትንቅንቅ በተለያዩ የአውሮፓ ግዙፍ ስታዲየሞች በባውዛ ደምቆ ሲከናወን የቆየው የክለቦች ትልቁ የውድድር መድረክ የሆነው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በፓሪስ ሴንት ጄርሜን እና በአርሰናል መካከል የሚከናወን ይሆናል። እኛም ምንም ጥርጥር በሌለው መልኩ የዛሬውን የስፖርት ሜዳ ጥንቅራችንን በዚህ ተጠባቂ እና አጓጊ መርሃ ግብር ላይ ለማድረግ ወደድን፤ አብራችሁን ቆዩ።
በዛሬው ዕለት የሚከናወነው 71ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሲሆን፣ ውድድሩ ስያሜውን ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከቀየረ በኋላ ደግሞ የዘንድሮውን ለ34ኛ ጊዜ ያደርገዋል። ከአምና ጀምሮ ይህ የውድድር ምዕራፍ ለየት ባለ መልኩ ተሳታፊ ቡድኖችን ወደ 36 ከፍ አድርጎ የሊግ ባህሪ እና የጨዋታ ቅርፅን ይዞ የቀረበ ሲሆን፣ አንድ ቡድን በሜዳው አራት ጊዜ እንዲሁም ከሜዳው ውጪ አራት ጊዜ ጨዋታውን አድርጎ በሚያገኘው ነጥብ መሠረት ቀድመው የሚያልፉ ስምንት ቡድኖች በቀጥታ በጥሎ ማለፍ ቋት ውስጥ ይገባሉ። ከ9ኛ እስከ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖች ደግሞ በደርሶ መልስ ጨዋታቸውን አድርገው ከሚለዩ ስምንት ቡድኖች ጋር በጥሎ ማለፉ እንዲገናኙ በሚል ባመጣው አዲስ የአጨዋወት መንገድ መሠረት የተከናወነ የውድድር ምዕራፍ ነው። ይህ አዲስ አሠራር በእግር ኳስ ወዳዱ ቤተሰብ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ባይቻልም፣ የውድድሩ ተወዳጅነት እና ተጠባቂነቱ ሳይቀዘቅዝ ለግዙፉ ዋንጫ ሁለቱን ታላላቅ ክለቦች አፋጥጧል።
ፓሪስ ሴንት ጄርሜን ይህንን ዋንጫ ከዓመታት ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ አምና ያሳካው ሲሆን፣ ዘንድሮም ድሉን ለመድገም ነው ወደ ሜዳ የሚገቡት። የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በበኩሉ በታሪኩ ይህንን ባለ ግዙፍ ጆሮ ዋንጫ እስካሁን አሳክቶት አያውቅም። መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የደረሱት በ2006 የውድድር ዘመን ሲሆን፣ በወቅቱ በስታድ ዴ ፍራንስ ስታዲየም በባርሴሎና 2 ለ 1 በመሸነፍ ዋንጫውን ማጣታቸው ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ እዚህ ምዕራፍ ላይ ሲገኙ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ዋንጫውን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል። ሁለቱም ቡድኖች ቀደም ባሉ ዓመታት ለፍፃሜው ደርሰው ዋንጫውን በማጣት ቅስማቸው ሲሰበር አይተውታል። የፈረንሳዩ ሀያል ቡድን ፒኤስጂ በ2020 በባየር ሙኒክ ሲሸነፍ፣ አርሰናሎች በበኩላቸው በ2006 በባርሴሎና በመሸነፍ ዋንጫውን ጨብጠው የለቀቁ በመሆናቸው፣ ይህ አይተው የተነፈጉ ቡድኖች የሚያደርጉት ትንቅንቅ ከወዲሁ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ ስቧል።
ከዚህ ጨዋታ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ቁልፍ የሆኑ ቁጥራዊ መረጃዎችን ለመመልከት ያህል፣ አሰልጣኝ ልዊስ ኤንሪኬ በ2014/15 የውድድር ዘመን ከባርሴሎና ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ማሳካት የቻለ ሲሆን፣ አምናም ከፓሪስ ጋር ይህንን ዋንጫ በማንሳት በታሪክ ሁለት የተለያዩ ክለቦችን በመያዝ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ክብርን ማሳካት የቻለ ሰባተኛው አሰልጣኝ መሆኑ ይታወሳል። ዘንድሮም ይህንን ክብር ደግሞ በማሳካት ከዚነዲን ዚዳን በመቀጠል ለተከታታይ ሁለት ዓመታት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ከአንድ ቡድን ጋር ማሳካት የቻለ ሁለተኛው አሰልጣኝ ለመባል ጥረት ያደርጋል። ስፔናዊው አሰልጣኝ ልዊስ ኤንሪኬ በአሰልጣኝነት ሕይወቱ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የደረሰበት ሦስተኛ ጨዋታውን ዛሬ የሚያከናውን ሲሆን፣ ድል ከቀናው ከዚነዲን ዚዳን፣ ቦብ ፔስሊ እና ፔፕ ጋርዲዮላ ተርታ የሚሰለፍበት ዕድል ይኖረዋል። እንዲሁም ዛሬ ድል የሚቀናው ከሆነ ከ1955 በኋላ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ሻምፒዮንስ ሊግን ማሳካት የቻለ ድንቅ አሰልጣኝ የሚባል ይሆናል። ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን ክብር ያሳካው ሆዜ ቪላሎንጋ ሲሆን፣ በ1955/56 እና በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1956/57 የውድድር ዘመን ሻምፒዮንስ ሊጉን ማሳካቱን የታሪክ ምህዳሮች ያመላክታሉ። ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ቡድን በሻምፒዮንስ ሊጉ ለተከታታይ ሁለት ጊዜ የነገሰው ሪያል ማድሪድ ሲሆን፣ ይህም በ2016/17 እና 2017/18 የውድድር ዘመን እንደነበር ይታወሳል።
ይህንን ታላቅ መርሃ ግብር የምታስተናግደው የአውሮፓዊቷ ሀገር የሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ስትሆን፣ ጨዋታውም በአንጋፋው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም የሚከናወን ይሆናል። ሁለቱ ቡድኖች አምና በውድድሩ የግማሽ ፍፃሜ ላይ የተገናኙ ሲሆን፣ በደርሶ መልስ ጨዋታ ፒኤስጂ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ፍፃሜው ማለፉ ይታወሳል። ሚኬል አርቴታ ይህንን ሽንፈት ለመበቀል ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን፣ አንድ ድንጋይ ለተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ያደናቅፈዋል ወይስ አይያደናቅፈውም የሚለውም በዚህ ጨዋታ የሚታይ ይሆናል። አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የሀገር ውስጥ የፕሪሚየር ሊግ ክብርን ካሳካ ማግስት፣ ይህንን ታላቅ ድል በሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ ድርብ ድል (Double Trophy) ለመጎናጸፍ የሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በትልቁ ይጠበቃል።
ፓሪስ ሴንት ጄርሜን በአምናው የጨዋታ ቀመር የተቃኘ፣ ነፃ የሆነ የአጨዋወት ፍሰት እንዲሁም እጅግ አስፈሪ የፊት መስመር ያለው ቡድን ሲሆን፣ በዚህ የውድድር ምዕራፍ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 44 ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። በዛሬው ጨዋታ አንድ ጎል ማስቆጠር የሚችሉ ከሆነ፣ በ1999/2000 የውድድር ዘመን በባርሴሎና ተይዞ የነበረውን በአንድ የውድድር ዘመን 45 ጎል የማስቆጠር ታሪካዊ ሪከርድ የሚጋሩ ይሆናል። በሻምፒዮንስ ሊጉ 10 ጎል አስቆጥሮ 6 ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ጆርጂያዊው ነበልባል ቪቻ ክቫራትስhelixያ የዚነዲን ዚዳንን በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል ለፓሪስ የማስቆጠር ክብረ ወሰን የተጋራ ሲሆን፣ ከጥሎ ማለፉ ጀምሮ በሱ ደረጃ በርካታ የጎል ተሳትፎ ያለው ሌላ ተጫዋች የለም። ሌላው በሻምፒዮንስ ሊጉ 7 ጎሎችን ያስቆጠረው የአምናው የባሎንዶር አሸናፊ ኡስማን ዴምቤሌም በዛሬው ጨዋታ ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ተጋጣሚያቸው አርሰናሎች የአጨዋወት ዘዬአቸው ከፒኤስጂ ፍጹም ተቃራኒ ነው። የመጀመሪያዎቹን ስምንት ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፎ ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀ ቡድን የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ ወዲህ ግን ከኳስ ውጪ በጣም የተረጋጋ፣ ለተጋጣሚ እጅግ ፈታኝ የሆነ አደረጃጀት ያለው የኋላ መስመር ባለቤት መሆን ችሏል። በዚህ የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ምዕራፍ አንድም ጨዋታ አለመሸነፋቸው በራሱ የሚናገረው ነገር ብዙ ነው። ባደረጓቸው 14 ጨዋታዎች የተቆጠረባቸው 6 ጎል ብቻ መሆኑ ደግሞ የተከላካይ መስመራቸው ከአለት የጠነከረ መሆኑን በግልፅ ያሳያል። ፓሪስ ሴንት ጄርሜን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከጥሎ ማለፍ አንስቶ ያደረጋቸውን ያለፉትን 64 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ አልቻለም። ስለዚህ የዛሬውም ጨዋታ በአንዳቸው አሸናፊነት የመጠናቀቅ ዕድሉ ሰፊ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዲሰጥ ምክንያት ሆኗል።
ሁለቱ ቡድኖች በሻምፒዮንስ ሊጉ እርስ በእርስ በተገናኙባቸው ያለፉት ሰባት አጋጣሚዎች እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ የተሸናነፉ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ተከባብረው በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። የፈረንሳዩ ሀያል ቡድን በእንግሊዝ ቡድኖች ላይ እያስመዘገበ ያለው ውጤት በዛሬውም ጨዋታ ላይ የስነ ልቦና የበላይነት ይዘው እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ዘንድሮ ብቻ ቼልሲ እና ሊቨርፑልን ከውድድሩ ያሰናበቱ ሲሆን፣ አምና ደግሞ ሊቨርፑል፣ አስቶን ቪላ እና አርሰናልን ከውድድሩ ማሰናበታቸው ይታወሳል። በአንጻሩ አርሰናል ፓሪስ ሴንት ጄርሜንን በአውሮፓ መድረክ የጥሎ ማለፍ ውድድር ማሸነፍ የቻለው ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1993/94 አውሮፓውያን የዋንጫ አሸናፊዎች ዋንጫ (የቀደመው ስያሜ) የውድድር ምዕራፍ ላይ እንደነበር የታሪክ ምህዳሮች ያመላክታሉ።
ፓሪስ ሴንት ጄርሜን በሻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክ ለፍፃሜ ውድድር ሦስት ጊዜ መቅረብ የቻሉ የመጀመሪያው የፈረንሳይ ቡድን መሆን ችለዋል። ክለቡ በ2019/20 የውድድር ዘመን በባየር ሙኒክ 1 ለ 0 ተሸንፎ ዋንጫውን ቢያጣም፣ በአንጻሩ አምና በዋንጫ ጨዋታ ታሪክ ከፍተኛውን የጎል ብዛት ያስቆጠረ ቡድን በመሆን ኢንተር ሚላንን 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የዚህን ታላቅ ዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወሳል። ፒኤስጂ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከእንግሊዝ ተወካይ ቡድኖች ጋር ባደረጋቸው ያለፉት 12 ጨዋታዎች ውስጥ በአንዱ ብቻ ሲሸነፍ፣ በዘጠኙ ድል ቀንቶታል እንዲሁም በሁለቱ አቻ ተለያይቷል። በክለቡ በኩል ዊሊያን ፓቾ፣ ቪቲንሀ፣ ዋረን ዛየር ኤምሬ እና ኑኖ ሜንዴዝ የፒኤስጂን ሁሉንም 16 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ሙሉ በሙሉ ተሰልፈው የተጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው። በሌላ በኩል በ21 ዓመት ከ245 ቀናት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ጆአዎ ኔቬዝ ዛሬ በቋሚነት የሚሰለፍ ከሆነ፣ በሻምፒዮንስ ሊጉ 40 ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለ ከቡድን አጋሩ ዛየር ኤምሬ እና ከጁድ ቤሊንጋም በመቀጠል በዕድሜ ትንሹ ሦስተኛው ተጫዋች የመሆን አዲስ ታሪክ ይጽፋል።
ከአርሰናል ጋር የተያያዙ ቁጥራዊ መረጃዎችን ስንመለከት ደግሞ መድፈኞቹ በ2005/06 የውድድር ዘመን በባርሴሎና 2 ለ 1 ከተሸነፉ በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሲበቁ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። ይህ ስኬት መድፈኞቹን ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ለሻምፒዮንስ ሊጉ ፍፃሜ መብቃት የቻሉ አምስተኛው የእንግሊዝ ቡድን ያደርጋቸዋል። ባለፉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ ሁለት ጊዜ፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑል ደግሞ አንድ አንድ ጊዜ ፍፃሜው ላይ መድረስ መቻላቸው ይታወሳል። አርሰናሎች ዛሬ ዋንጫውን ማሳካት ከቻሉ ከአስቶን ቪላ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ፣ ኖቲንጋም ፎረስት እና ማንቸስተር ዩናይትድ በመቀጠል ይህንን ክብር ያገኘ ሰባተኛው የእንግሊዝ ቡድን መሆን ይችላሉ።
በተጨማሪም መድፈኞቹ ሻምፒዮንስ ሊጉን ማሳካት ከቻሉ የውድድሩ 25ኛው አዲስ የዋንጫ ባለቤት ቡድን መሆን ይችላሉ። አምና ፒኤስጂ ዋንጫውን ሲያሳካ 24ኛው አዲስ ቡድን እንደነበር ይታወሳል። በታሪክ ተከታታይ በሆነ መንገድ ውድድሩን አሳክተው የማያውቁ አዳዲስ ቡድኖች በተከታታይ ዋንጫውን ያነሱት በ1991/92 እና 1992/93 የውድድር ዘመን ላይ ሲሆን፣ በወቅቱ ባርሴሎና ሳምፕዶሪያን እንዲሁም ማርሴ ኤሲ ሚላንን በመርታት ዋንጫውን መውሰዳቸው ይታወሳል። አርሰናል የሀገር ውስጥ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ከ22 ዓመታት በኋላ ማሳካቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዛሬ የሻምፒዮንስ ሊጉን ድል ከደገሙ ደግሞ በታሪክ ይህንን የድርብ ክብር (Double Trophy) ማሳካት የቻሉ አራተኛው የእንግሊዝ ቡድን ይሆናሉ። ከዚህ ቀደም ሊቨርፑል በ1976/77 እና 1983/84፣ ማንቸስተር ዩናይትድ በ1998/99 እና በ2007/08 እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ በ2022/23 ይህንን ድርብ ድል ተቀናጅተዋል።
መድፈኞቹ በዚህ የሻምፒዮንስ ሊግ የውድድር ምዕራፍ ባደረጓቸው 14 ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት አላስተናገዱም፤ በዚህ ደረጃ ጠንክረው የተጓዙበት ሌላ የውድድር ምዕራፍ በታሪካቸው የለም። ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል በዘጠኙ ምንም ጎል አላስተናገዱም፤ በዛሬው ጨዋታም መረባቸውን ካላስደፈሩ የራሳቸውን የ2005/06 የውድድር ዘመን ታሪክ እንዲሁም ሪያል ማድሪድ በ2015/16 ያሳካውን አስደናቂ ሪከርድ የሚጋሩ ይሆናል። ዋንጫውን ዛሬ ካሳኩም በሻምፒዮንስ ሊጉ ታሪክ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፉ ድሉን የጨረሱ 10ኛው ቡድን የሚባሉ ሲሆን፣ ከአምና ጀምሮ በተተገበረው አዲሱ የአጨዋወት ህግና አወቃቀር መሠረት ከሆነ ግን የመጀመሪያው ታሪካዊ ቡድን የመሆን ዕድል ይኖራቸዋል።
የአርሰናሉ ስፔናዊ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከስፔን ውጭ የሚገኝ ቡድንን በመያዝ በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ መድረስ የቻለ አራተኛው ስፔናዊ አሰልጣኝ ሆኗል። ከእሱ በፊት ራፋ ቤኒቴዝ ከሊቨርፑል ጋር፣ ፔፕ ጋርዲዮላ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር እንዲሁም የዛሬው ተጋጣሚው ልዊስ ኤንሪኬ ከፓሪስ ሴንት ጄርሜን ጋር ለፍፃሜው መድረስ ችለዋል። አርሰናሎች ዘንድሮ 29 የተለያዩ ተጫዋቾችን በሻምፒዮንስ ሊጉ የተጠቀሙ ሲሆን፣ ጋብሪዬል ማርቲኔሊ እና ግብ ጠባቂው ዴቪድ ሬያ 13 ጊዜ በመሰለፍ በርካታ ጨዋታዎችን ያደረጉ ተጫዋቾች ናቸው። በሌላ በኩል ማይልስ ልዊስ ስኬሊ በ19 ዓመት ከ246 ቀኑ ዛሬ መሰለፍ ከቻለ፣ ጁድ ቤሊንጋምን በመከተል 20 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለ በዕድሜ ሁለተኛው ትንሹ ተጫዋች የሚባልበትን አዲስ ሪከርድ በእጁ ያስገባል።
ከቡድን ዜናዎች ጋር በተያያዘ በፕሪሚየር ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ከክሪስታል ፓላስ ጋር መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት የነበረው ማዱኤኬ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ሲታወቅ፣ ቤን ዋይት ግን ለዚህ ጨዋታ የማይደርስ ይሆናል። ትልቁ ጥያቄ ለሁለት ወራት ያህል ከሜዳ የራቀው የጁሪየን ቲምበር ጉዳይ ሲሆን፣ የመጨረሻውን የሀኪም ውሳኔ እየጠበቀ ይገኛል። ሆኖም የጨዋታ ብቃቱ (Match fitness) ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ ጨዋታውን በቋሚነት ላይጀምር እንደሚችል ወይም በቋሚነት ቢጀምር እንኳ ቶሎ ተቀይሮ ሊወጣ እንደሚችል የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ። በፒኤስጂ በኩል ኡስማን ዴምቤሌ ከ11 ቀናት በፊት መጠነኛ የጡንቻ መሳሳብ አጋጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝና ጨዋታውን በቋሚነት እንደሚጀምር ይጠበቃል። ሞሮኮአዊው አሽራፍ ሀኪሚ ለአንድ ወር ከሜዳ ያራቀውን የጭን ጡንቻ መሳሳብ ህመም አገግሞ በግሉ ልምምድ እያደረገ ቢሆንም፣ 90 ደቂቃ ሙሉ ለመጫወት የሚያስችል የአካል ብቃት ላይ ባለመሆኑ የመሰለፉ ነገር እጅግ አጠራጣሪ ሆኗል።
ይህ ጨዋታ የፈረንሳይ እና የእንግሊዝ ተወካይ ቡድኖች የሚያደርጉት የመጀመሪያው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ከመሆኑም በላይ፣ ሁለት ስፔናውያን አሰልጣኞች የተለያየ የውጭ ሀገር ክለብ ይዘው በሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሲገናኙ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደርገዋል። ጨዋታው የሚካሄድበት የሀንጋሪው ፑሽካሽ አሬና ስታዲየም የ2023 የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሲቪያ የጆዜ ሞሪንሆውን ሮማ በመለያ ምት አሸንፋ ዋንጫውን የወሰደችበት እንዲሁም በ2020 የዩኤፋ ሱፐር ካፕ ላይ ባየር ሙኒክ ከኋላ ተነስቶ ሲቪያን 2 ለ 1 ያሸነፈበት ታሪካዊ ስታዲየም ነው።
ከጨዋታው መጀመር በፊት “The Killers” የተሰኘው ታዋቂው የአሜሪካ ኢንዲ ሮክ ባንድ “Mr. Brightside”፣ “Human” እንዲሁም “When You Were Young” የተሰኙ ተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በስታዲየሙ ለታደሙና በመላው ዓለም በቀጥታ ስርጭት ለሚከታተሉ የእግርኳስ አፍቃሪያን ያቀርባል። የሻምፒዮንስ ሊጉን ይፋዊ መዝሙር (Official Anthem) ደግሞ በቡዳፔስት የተወለደው ታዋቂው ሀንጋሪያዊ የኮንሰርት ፒያኒስት አዳም ጂዮርጂ በቀጥታ የፒያኖ አቀራረብ የሚያቀርበው ይሆናል። ይህ የሙዚቃ ባለሙያ ከዚህ ቀደም በ2023 የኢስታንቡሉ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ላይ መዝሙሩን በሚገባ ማቅረቡ ይታወሳል።
ታዲያ ማን ያሸንፍ ይሆን? ፓሪስ ሴንት ጄርሜን ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ የአውሮፓን የንግስና ዘውድ ይደፋል ወይስ መድፈኞቹ አርሰናሎች በ140 ዓመት የእግርኳስ ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን ታላቅ ዋንጫ ከፍ አድርገው ያሳካሉ የሚለው ጥያቄ መላው ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ ሆኗል። ጀርመናዊው ዳኛ ዳንኤል ሲበርት በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ይህ ታላቅ ጨዋታ ምሽት 4:00 ሰዓት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ምሽት 1:00 ሰዓት) በፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ይጀምራል።
በሚካኤል ደጀኔ
ምላሽ ይስጡ