ግንቦት 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዘገባ ሥራ ለሚያከናውኑ 1 ሺህ 814 ጋዜጠኞች እና ለ22 ሺህ የፓርቲ ወኪሎች መለያ መስጠቱን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
ለ64 ተቋማት ለተውጣጡ በአጠቃላይ ለ1 ሺህ 814 ጋዜጠኞች መለያ መስጠቱን የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ገልጸዋል፡፡
የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 114 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ዋና ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል። ድጋፉ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከአውሮፓ ኅብረት የተገኘ ሲሆን፣ ቦርዱ ከመንግሥት የበጀት ድጋፍም መጠቀሙን ገልጿል።
በተጨማሪም 55 ያህል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በታዛቢነት ሥራ ላይ ፈቃድ ተሰጥቷቸው መቆየታቸውንና የታዘቡትን ከተለያዩ አካባቢዎች ለቦርዱ ሪፖርት ማድረጋቸውን ዋና ሰባሳቢዋ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ቦርዱ በእንቅስቃሴው ውስጥ እስካሁን ባለው ሂደት ከውጭ ድጋፍ 7 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን ዋና ሰብሳቢዋ የገለጹ ሲሆን፣ ይህም ከእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ስፔን፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ እና ጃፓን ከመሳሰሉ አጋር ሀገራት የተገኘ ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል።
አያይዞም ቦርዱ በቅድመ ምርጫ ሥራው በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ፓርቲዎችን ወክለው የሚንቀሳቀሱ ወኪሎችን በመመዝገብ መለያ መስጠቱን አስታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ