በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ በሕገ-ወጥ ደላሎች ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ተታልለው ለከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰትና ለሕይወት ማጣት አደጋ እንደሚጋለጡ ተመላሾችና የዘርፉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ሕገ-ወጥ ደላሎች የፍልሰት ሂደቱን “በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚያጠናቅቅ ፈጣን መንገድ” አድርገው በማቅረብ ማኅበረሰቡን እንደሚያታልሉ የሚገልጹት ባለሙያዎች፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር መዳረሻ ሀገር ላይ ሲደረስ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ጥበቃ አልባ የሚያደርግ “የፈጣን አደጋ ወጥመድ” መሆኑን ያመለክታሉ።

የምሳሌ” ሪተርንስ ኤንድ ፖቴንሻል ማይግራንት አርት ኦርጋናይዜሽን መስራችና ስራ አስኪያጅ ሕይወት ዳግም፣ የደላላውን አሠራር ልክ እንደ ፈጣን ምግብ (Fast Food) ይመስሉታል። ፈጣን ምግብ ለአጭር ጊዜ ረሃብን አስታግሶ ፊትን ቢያፋፋም ቆይቶ ጤናን እንደሚያበላሸው ሁሉ፣ ደላሎችም መንግሥት ያዘጋጀውን የ21 ቀን የግንዛቤና የክህሎት ሥልጠና ወደ 7 ቀን በማሳነስ ዜጎችን ያለ ምንም ቅድመ-ዝግጅት እንደሚልኩና ይህም መድረሻ ሀገር ላይ ለሚፈጠር ከፍተኛ ግራ መጋባትና እንግልት ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ሕይወት ዳግም ያስረዳሉ።

በፍልሰት ስም በቀረበ የደላላ ስምምነት ተታልሎ የ21 ቀን ሥልጠና ሰልችቶት ሂደቱን በሰባት ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ጓጉቶ የነበረው ወጣቱ ዳግም ዮሐንስ (ስሙ የተቀየረ)፣ የደላላው ፍጥነት የሕይወት አደጋ መሆኑን አሁን ላይ በሚገባ ተረድቷል። ዳግም ቀደም ሲል በመንግሥት በኩል የሚጠየቀው የሕክምና ምርመራ፣ የአሻራ መስጠትና የሥልጠና ሂደት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድበትና አድካሚ እንደሆነ ያስብ እንደነበር ያስታውሳል። ይሁን እንጂ ደላላውም ቢሆን ፓስፖርትና የሕክምና ምርመራዎችን ለማጠናቀቅ ከሦስት እስከ አራት ወራት በላይ ጊዜ የሚፈጅበት በመሆኑ፣ ፈጣን የተባለው የደላላ መንገድ በአጭር ጊዜ የመክበር “የእውር ድንብሩ” ጉዞ መሆኑንና ከዝቅተኛ ግንዛቤ የሚመነጭ የተስፋ ቃል መሆኑን አምኗል። በመንግሥት በኩል የሚደረገው ጉዞ የተወሰነ ጊዜና ሒደት ቢጠይቅም፣ የሥራ ውሉን አረጋግጦ፣ ደሞዝን ተስማምቶና አሠልጣኝ ተቋማትን በግልጽ ለይቶ የሚልክ በመሆኑ “ሞትን የመቀነስ ትልቅ ኃይል” እንዳለው በመረዳት፣ ሕጋዊውና አስተማማኙ መንገድ ብቻ የሕይወት ዋስትና እንደሚያስገኝ የውስጥ እምነቱን ይፋ አድርጓል።
ለ10 ዓመታት በፍልሰት መከራዎችን ያስተናገደችውና ከፍተኛ የሕይወት ውጣ ውረድ ያሳለፈችው ተመላሿ ፋጡማ መሐመድም(ስሟ የተቀየረ)፣ በሕገ-ወጥ መንገድ መጓዝ ዕድሜንና ወርቃማውን የወጣትነት ዘመን ከማባከን ባለፈ የሕይወት ዋስትና እንደማያስገኝ ትመሰክራለች። በተለይም በሕገ-ወጥ መስመር የሄዱ ዜጎች ከአንድ በላይ ቀጣሪዎች ጋር እየተቀያየሩ መከራ ካዩ በኋላም፣ ወደ ሀገር ተመልሰው በድጋሚ በሕገ-ወጥ መንገድ የመፍለስ “አባዜ” ሰለባ እንደሚሆኑና በኤምባሲዎች ውስጥ እንኳ ሳይቀር ጥቅማቸውን ለማሳደድ ከደላሎች ጋር የሚመሳጠሩ ጥቁር መረቦች መኖራቸውን ፋጡማ መሐመድ በቁጭት ይገልጻሉ። በተቃራኒው በመንግሥት ሥርዓት ቢኬድ ቀጣሪው ፈርሞና ተስማምቶ ስለሚወስድ ክፉ ነገር ሊያደርጉ እንደማይችሉ፣ ቢያደርጉ እንኳን በሕግ የመያዝ ባሕርይ እንዳለውና መብቶቻቸው እንደሚጠበቅ በተግባር ያየችውን ምስክርነት ትሰጣለች።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተወካዩ አቶ ተክሌ ቀደም ሲል የነበሩትን የአሠራር ክፍተቶችና መረጃ የማግኘት ችግሮችን ለመቅረፍ፣ አሁን ላይ አገልግሎቶቹን እስከ ታችኛው የወረዳና የክፍለ-ከተማ መዋቅር ድረስ ማውረዱን ይፋ አድርገዋል። ቀደም ሲል ከክልል ተነስተው ሂደቱን ለመጀመር አዲስ አበባ መምጣት ይገደዱ የነበሩ ዜጎች፣ አሁን ላይ ባሉበት አካባቢ በተቋቋሙት የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች (One-Stop Centers) በመጠቀም ምዝገባ መጀመር ይችላሉ ብለዋል። መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው “ELMIS” (Electronic Labour Market Information System) የተባለው ዘመናዊ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት፣ ዜጎች አሻራቸውን ሰጥተው፣ የሁለትዮሽ ስምምነት በተፈራረሙ ሀገራት ያሉ የሥራ አማራጮችን አጥርተው እንዲያውቁ ያደርጋል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 1278 መሠረት፣ ፍልሰት የዜጎች መብት እንደሆነ የተደነገገ ቢሆንም፣ ይህ መብት ተፈጻሚ መሆን ያለበት ግን በበቂ መረጃና በሕጋዊ ከለላ ላይ ተመስርቶ መሆን እንዳለበት ባለሙያዎች ያሳስባሉ። ዜጎች ከመነሳታቸው በፊት የመድረሻ ሀገራትን ባህል፣ የአየር ሁኔታ፣ የሥራ ባህልና የደሞዝ ሁኔታ በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል። በሕጋዊ መንገድ የሚጓዙ ሠራተኞች ከምግብ ጀምሮ የደሞዝ መከበርና የውል ስምምነት ጥበቃን ጨምሮ ሙሉ የሕግ ከለላ የሚኖራቸው ሲሆን፣ አቤቱታዎችን ለማቅረብና ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተል የተዘጋጁትን እንደ “ለመንገዴ” ያሉ የሞባይል መተግበሪያዎችን እና የቴሌብር ሲስተሞችን በመጠቀም ራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ታጋሽ መሆን፣ መረጃን ከመጠየቅ አለመፍራትና እዚሁ ሀገር ውስጥ ያሉትን የሥራ አማራጮች አእምሮን ሰፋ አድርጎ መመርመር፣ ዜጎችን ከአስከፊው የደላሎች ብዝበዛ ጠብቆ ቀጣይነት ያለውና አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን የሚዲያና የፍልሰት ባለሙያዎች በጥብቅ ያሳስባሉ። ዜጎች ስለ ሕጋዊ የሥራ ስምሪት ሂደቶች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፣ ጥቆማዎችን ለመስጠት ወይም ያጋጠሟቸውን እንግልቶች ለማመልከት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀውን የነፃ ጥሪ ማዕከል መስመር 8444 በመጠቀም መረጃ ማግኘትና ራሳቸውን ከብዝበዛ መጠበቅ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ