ሚያዚያ 15 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የቅርብ ጓደኛቸውን ህይወት በማጥፋት ሲያሽከረክር የነበረውን መኪና ወስደው የተሰወሩ ሁለት ግለሰቦች ከ23 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሰሜን ማዘጋጃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተገልጿል። ከአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ም/ጠቅላይ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሟች ገብረሚካኤል ሰይፉ የወንጀል ፈፃሚዎቹ የቅርብ ጓደኛ ነበር። በዕለቱ ሟች እስከ ምሽቱ 5 ሠዓት ድረስ ቴዎድሮስ ታከለ እና ሲሳይ ጥላሁን ከሚባሉ ጓደኞቹ ጋር አብሮ ሲዝናና ካመሸ በኋላ ወንጀለኞቹ አንገቱን በማነቅ ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጋቸውን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።
ተከሳሾቹ የሟቹን አስክሬን መንገድ ላይ በመጣል ሞባይል ስልኩንና መታወቂያውን እንዲሁም ሲያሽከረክር የነበረውን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 4-15624 ኢት የሆነ መኪና ዘርፈው ተሰውረው ነበር። ሆኖም ፖሊስ ባደረገው ያልተቋረጠ ክትትል አንደኛው ተከሳሽ ቴዎድሮስ ታከለ ከአየር ጤና አካባቢ፣ ሁለተኛው ተከሳሽ ሲሳይ ጥላሁን ደግሞ በሱሉልታ ከተማ በ24 ሰዓታት ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በተከናወነ ምርመራ፤ የሰረቁትን ተሽከርካሪ በሸገር ከተማ ወለቴ አካባቢ እንዲሸጥላቸው ለአንድ ግለሰብ የሰጡት መሆኑ ተረጋግጦ መኪናው እንዲመለስ ተደርጓል። ፖሊስ በሰውና በሰነድ ማስረጃ አደራጅቶ ባቀረበው ክስ መሠረት ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
በዚህም መሠረት ቴዎድሮስ ታከለ በ25 ዓመት፣ ሲሳይ ጥላሁን ደግሞ በ23 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኖባቸዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ባስተላለፈው መልዕክት፤ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚፈፀም ማንኛውም የወንጀል ድርጊት ከፖሊስና ከህብረተሰቡ ዓይን እንደማያመልጥ ገልጾ፣ ወንጀል ፈፃሚዎች ከመሰል ድርጊት እንዲታቀቡ አሳስቧል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ