ሚያዚያ 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ የጀመሩት “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” እና “ሠላም ለኢትዮጵያ ጥምረት” በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ አለመሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ባለፈው መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ማኒፌስቶውን በማስተዋወቅ በይፋ የምርጫ ቅስቀሳ የጀመረ ቢሆንም፣ ከዚያ ቀን ውጪ በተለያዩ ምክንያቶች ቅስቀሳ እያደረገ አለመሆኑን የትብብሩ ምክትል የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ ታጠቅ አሰፋ ተናግረዋል። በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ እጥረት፣ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች በአስተዳደሪዎች የሚደረግ ተጽዕኖ ለምርጫ ቅስቀሳ ምቹ ምህዳር እንዳይኖር ማድረጉን ገልጸዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና በምርጫ ቦርድ በየምርጫ ጣቢያዎቹ በተዋቀሩ አቤቱታ ሰሚዎች አማካኝነት ችግሩን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም፣ ከቀረው ጊዜ አንጻር በሚፈለገው ልክ ምላሽ እየተሰጠ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
የሠላም ለኢትዮጵያ ጥምረት በበኩሉ በክልሎች በሚፈለገው ልክ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ እንዳልቻለ የጥምረቱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳሮታ ጉምኢ ተናግረዋል። ጥምረቱ ከጋምቤላ ውጭ በሚወዳደርባቸው አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያደርግ ጫናዎች እየተደረጉበት መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ እንዲፈታ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ለምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውን በመግለጽ፣ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችለውን ኮሚቴ ማዋቀሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ከቦርዱ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ