መጋቢት 16 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር (ፔንታገን) በዓለም ላይ በፈጣን ደራሽነቱ የሚታወቀው 82ኛው የአየር ወለድ ክፍለ ጦር (82nd Airborne Division) አባላት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመሰማራት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ እንዲቆዩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ወታደራዊ ውጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ በተሸጋገረበት እና ጦርነቱ አራተኛ ሳምንቱን በያዘበት ወቅት ነው።
እንደ ወታደራዊ ምንጮች ገለጻ ወደ 3,000 የሚጠጉ የአየር ወለድ ወታደሮች የ”ፈጣን ደራሽ ኃይል” (Immediate Response Force) አካል በመሆን በማንኛውም ሰዓት ወደ ቀጠናው ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ናቸው።
ይህ ኃይል ትዕዛዝ በደረሰው በ18 ሰዓታት ውስጥ በማንኛውም የዓለም ክፍል የመድረስና ስልታዊ ቦታዎችን የመቆጣጠር ልዩ ብቃት አለው።
የዚህ ጦር ዋነኛ ተልእኮ በኢራን ቁጥጥር ስር ያለውን እና የዓለም የነዳጅ ንግድ ቁልፍ መስመር የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ስምጥ ወሽመጥ ደህንነት ማስጠበቅ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በተለይም የኢራን ዋነኛ የነዳጅ መውጫ በሆነችው የኻርግ ደሴት (Kharg Island) አካባቢ ሊኖር የሚችለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመምራት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ ወታደሮቹ እስካሁን በይፋ ባይሰማሩም ለማንኛውም ዓይነት ጥቃትና ስልታዊ እርምጃ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል ቴህራን የአሜሪካን ወታደራዊ ዝግጅት “የስነ-ልቦና ጦርነት” በማለት የፈረጀችው ሲሆን በቀጠናው ለሚፈጠር ለማንኛውም ግጭት አሜሪካ ተጠያቂ እንደምትሆን አስታውቃለች።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) በኢራን ውስጥ በሚገኙ የድሮን ማምረቻዎች እና የሚሳኤል ጣቢያዎች ላይ የአየር ጥቃቱን የቀጠለ ሲሆን የአየር ወለድ ጦሩ መሰማራት ግን ጦርነቱ ወደ መሬት ላይ ውጊያ ሊሸጋገር እንደሚችል ትልቅ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ