በቀደምት ጊዜ ሃገር በጠላት እጅ እንዳትወድቅ ለመከላከል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አርበኞች ከፍተኛ መስዋት የከፈሉበትን ቀን ለመዘከር የአርበኞች ቀን በዛሬው ዕለት በሃገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።
በሃገራችን ታሪክ አርበኞች ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጣቸው የሚገልጹት የታሪክ ባለሙያው አቶ በላይ ስጦታው የአርበኞችን ታሪክ ከመረዳት እና ከማስቀጠል አንጻር አሁን ላይ ያለው ትውልድ ክፍተት እንደሚስተዋልበት ተናግረዋል።
ታሪክን በአግባቡ ከመሰነድ እና ትውልዱን ከማስተማር አንጻር በትኩረት አለመሰራቱ እንዲሁም ለፖለቲካ መጠቀሚያ መደረጉ ትውልዱ ለሃገር ዋጋ የከፈሉ አርበኞችን ታሪክ እንዳያውቅ ብሎም የተዛባ የታሪክ አረዳድ እንዲኖረው አድርጓል ይላሉ።
በመሆኑም ትውልዱ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን እየተስተዋሉ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እንደሃገር ለአርበኞች ታሪክ ትኩረት ሰጥቶ ማስተማርና ማስገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በማህበረሰብ ግንባታ ሂደት የሃገርን ባህል፤ እሴት፤ ታሪክ ማስተማር እና ማስቀጠል የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚገልጹት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር አዲስ ዜና ናቸው።
አሁን ላይ በትውልዱ የሚስተዋለው ክፍተት በሌሎች ሃገራት ባህልና ታሪክ ተጽዕኖ ስር መውደቅ፤ ቀደምት አርበኞች ለሃገር የነበራቸውን ሁለንተናዊ አረዳድ ዋጋ ያለመስጠት እንዲሁም ፖለቲካዊ ስርዓቱ የፈጠረው ክፍተት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህም የደበዘዘ ሃገራዊ ስሜት እንዲፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ ለትውልድ ግንባታ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለሃገር ዋጋ የከፈሉ አርበኞችን ታሪክ ለትውልዱ በማስተማር ሒደት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ አርበኞች፤ የታሪክ ምሁራን፤ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን ማህበረሰቡም በራሱ ጥረት በማድረግ የማወቅ ድርሻና ኃላፊነት እንዳለው ተመላክቷል።
ምላሽ ይስጡ