መስከረም 07 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ) በማር ምርት ላይ የሚታየውን የጥራት መጓደል፣ ከሌላ ምርት ጋር ቀላቅሎ ለገበያ የማቅረብ ችግር እና ያለ ህጋዊ ፈቃድ የሚከናወን ግብይትን ማስቀረት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር መቅረቡን ተቋሙ አስታውቋል፡፡ ረቂቅ መመሪያው ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በዝግጅት ላይ የቆየ ሲሆን፤ በግብርና ሚኒስቴር የማኔጅመንት አባላት ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ በዘርፉ ሰፊ የህግ ማዕቀፍና የቁጥጥር ስልጣን የሚፈጥር እንደሆነ እና ህጋዊ አሰራርን ከተከተሉ አምራቾችና አቅራቢዎች ውጭ ያሉትን ያልተገቡ ተወዳዳሪዎች ከገበያ የሚያስወጣ መሆኑን በሚኒስቴሩ የንብና የሀር ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ አዚዝ አያሌው ተናግረዋል፡፡ ከህግ ማዕቀፉ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ከቁጥጥር ባለስልጣኑ ጋር በመተባበር ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራር መዘርጋቱን በመጥቀስ፤ በዚህም ማንኛውም ማር አቅራቢ ምርቱን ወደ ገበያ ከማስገባቱ በፊት ህጋዊ የንግድ ፈቃድ እንዲኖረው ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ምርቱም በላቦራቶሪ ተፈትሾ የጥራትና የደረጃ ማረጋገጫ እንደሚሰጠው እና መስፈርቱን አሟልተው ጥራታቸው ለተረጋገጠ ምርቶች ልዩ የQR ኮድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ ለገበያ የቀረበው ማር የተቀየጠ እና የጥራት ችግር ያለበት ከሆነ መተግበሪያው ወዲያውኑ ውድቅ እንደሚያደርገው በመግለጽ፤ አጠራጣሪው ምርት የሚገኝበትን ቦታ በጂፒኤስ መረጃ በመታገዝ ለተቆጣጣሪው ባለስልጣንም ሆነ ለደረጃዎች ኢንስቲትዩት በቀጥታ ጥቆማ የሚቀርብበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ በሙከራ ደረጃ የሚገኘው አሰራር በጥቂት አቅራቢዎች ላይ ተሞክሮ ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ በሙሉ አቅም ወደ ስራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ አዲሱ አሰራር ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የማር ምርት መጠን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ