መስከረም 07 ቀን 2019ዓ.ም.(መናኸሪያ ) በአዲስ አበባ ከተማ እያደገ የመጣውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት እና ያለውን የአቅርቦት ክፍተት ለማሻሻል የአጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል። በ2018 በጀት ዓመት በቦሌ አራብሳ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና በሌሎች አካባቢዎች 20 አዳዲስ ጉድጓዶች ተቆፍረው ስራ በመጀመራቸው በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውሃ ወደ ሲስተም ማስገባት መቻሉን የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰርካለም ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ በ2019 በጀት ዓመት 130 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መስጠት የሚያስችል የከርሰ ምድር ውሃ የማልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ያህሉ ባለፉት 2 ዓመታት ሲገነባ የቆየው የጨቋላ የውሃ ፕሮጀክት እንደሆነና ቀሪው 30 ሺህ ሜትር ኪዩብ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎች ከሚቆፈሩ ጉድጓዶች የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በቀን ከ500 ሺህ እስከ 600 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማመንጨት አቅም ያላቸው የሲቢሉ እና የአለልቱ ችዳሮቤ የገጸ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶች ጥናት ተጠናቆ ገንዘብ የማፈላለግ ስራዎች በተጎዳኝ እየተከናወኑ መሆናቸውን ወ/ሮ ሰርካለም ገልጸዋል፡፡ የከተማዋን የውሃ ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት አዳዲስ ምንጮችን ከማልማት ጎን ለጎን የሚመረተው ውሃ እንዳይባክን የመጠበቅና የውሃ ሀብቱን በአግባቡ የመጠቀም ስራ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል። በ2018 በተሰራው ስራ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ አመላክተዋል።
___
ሀሳብ እና‘ሳ‘ፍራለን
ምላሽ ይስጡ